Wazema Media / Radio Canali Telegram

Wazema Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com

View in Telegram

Recent Posts

ለቸኮለ! ዓርብ ሚያዝያ 18/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የይገባኛል ውዝግብ በሚነሳባቸው ራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፍላ ወረዳዎች በአካባቢዎቹ ማኅበረሰቦች መካከል እየተካረረ የሄደው ውጥረት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ዛሬ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ፋኪ፣ ኹሉም ወገኖች ግጭት እንዲያቆሙ እና የዜጎችን ዳግም መፈናቀል ለማስቀረት የሲቪሎች ደኅንነት እንዲጠበቅ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። ፋኪ፣ የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት እንዲከበር እና ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር እንዲኹም በግጭት ማቆም ስምምነቱ ላይ በተገለጠው መሠረት የአወዛጋቢ አካባቢዎችን ጉዳይ ለመፍታት የፖለቲካ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አድርገዋል።

2፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በከተማዋ የመንገድ ኮሪደር ልማት ሳቢያ ከሠፈራቸው ለተነሱ ከ4 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ካሳ እንደተከፈላቸው ዛሬ ለከተማዋ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ፣ በአምስቱ የመንገድ ኮሪደር መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች እስካሁን 5 ሺህ 135 ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው እንደተነሱና ወደ ሌላ ቦታ እንደተዛወሩ ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል። ከንቲባዋ፣ በመንገድ ኮሪደር ልማቱ ለተነሱ 307 የንግድ መደብሮች፣ አስተዳደሩ ለካሳ ክፍያ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መመደቡንና 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካሳ እንደተከፈለ ጭምር አብራርተዋል።

3፤ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ፣ አፍሪካ ኅብረት የባንክ የውጭ ምንዛሬ ሒሳቡን ወደ ሌላ አገር ሊያዘዋውር አስቧል ተብሎ የተሠራጨው መረጃ "የተሳሳተ ነው" በማለት ተናግረዋል። ቃል አቀባይ ነቢዩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ሚንስቴሩ ከኅብረቱ ጽሕፈት ቤት ጋር ባደረገው ውይይት ተቋሙ የባንክ ሒሳቡን ወደ ሌላ አገር የማዘወር ሃሳብ እንዴሌለው ሃላፊዎቹ አረጋግጠዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ቀሲስ በላይ መኮንን፣ ከአፍሪካ ኅብረት የንግድ ባንክ ሒሳብ ውስጥ ግማሽ ቢሊዮን የሚገመት ብር ለማውጣት መሞከራቸውን ተከትሎ፣ ኅብረቱ የውጭ ምንዛሬ ሒሳቡን ወደ ሌላ አገር ሊያዛውር እንዳሰብ ከድርጅቱ ሃላፊዎች መስማታቸውን ጠቅሰው እንዳንድ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበው ነበር።

4፤ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይና ጸጥታ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል፣ ኅብረቱ ለኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር መሾሙን አስታውቀዋል። ኅብረቱ ለኢትዮጵያ አምባሳደር አድርጎ የሾማቸው ፊንላንዳዊቷ ዲፕሎማት ኤመስበርገር ሶፊ ናቸው። ሶፊ ባኹኑ ወቅት በፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ዳይሬክተር ጀኔራል ኾነው በማገልገል ላይ ናቸው። ሶፊ ቀደም ሲል፣ የኅብረቱን የፖለቲካና ጸጥታ ኮሚቴ በሊቀመንበርነት መርተዋል። ኅብረቱ አዲስ ልዑክ የሾመው የሥራ ጊዜያቸውን በጨረሱት፣ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ምትክ ነው።

6፤ የሱማሊያ መንግሥት፣ አሜሪካ ያሰለጠነችውንና ድጋፍ የምታድርገለትን "ዳናብ" የተሰኘውን ልዩ ኮምንዶ የተወሰኑ አባላት ማሠሩን አስታውቋል። ቁጥራቸው ያልተገለጡ የልዩ ኮማንዶው አባላት መታሠራቸው የተሰማው፣ አሜሪካ ለልዩ ኮማንዶው የምትመድበው ምግብና ነዳጅ እየተሠረቀ ገበያ ላይ እንደሚሸጥ መረጃዎች ከወጡና አሜሪካም በዚኹ ሳቢያ የምግብ ድጋፏን ማቋረጧ ከተሠማ በኋላ ነው። ከአሜሪካ ልዩ ሥልጠና የተሰጠው ልዩ ኮማንዶ፣ አልሸባብን በመውጋት እውቅናን ያተረፈ የሱማሊያ ጦር ሠራዊት ክፍል ነው። አሜሪካ ለተጨማሪ ልዩ ኮማንዶዎች ማሰልጠኛ አምስት አዳዲስ ወታደራዊ ጦር ሠፈሮችን እንደምትከፍት ባለፈው የካቲት ገልጣ ነበር።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ8903 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 58 ብር ከ0281 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ9672 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ3265 ሳንቲም ኾኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ9864 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ2061 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ዓርብ ሚያዝያ 18/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ በቀድሞው የሰላም ሚንስትር ደዔታ ታዬ ደንድዓ ላይ ትናንት በፌደራሉ ፍርድ ቤት የወንጀል ክስ መመስረቱን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዓቃቤ ሕግ በታዬ ላይ የመሠረተው ክስ፣ "የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት" እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በይፋ "የድጋፍ መልዕክቶችን ማስተላለፍ" የሚል እንደኾነ ዘገባዎች አመልክተዋል። ፖሊስ በታዬ መኖሪያ ቤት ውስጥ በፍተሻ ወቅት የጦር መሳሪያ እንዳገኘ በመግለጽ፣ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ሕጉን ጥሰዋል የሚል ክስ ጭምር ተመስርቶባቸዋል ተብሏል።

2፤ የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መዘግየት አሳሳቢ ችግር ላይ መድረሱን ገልጧል። ፓርቲው፣ የየካቲት ወር የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ 80 በመቶ ብቻ እንደተከፈለና ከመጋቢት ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 15 ከሶዶ ከተማ ሠራተኞች በስተቀር የሌሎች የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞችም ደመወዝ ጨርሶ እንዳልተከፈላቸው ገልጧል። መምህራን ደመወዛቸው በመቋረጡና ሥራ በማቆማቸው፣ ከሚያዝያ የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ከ70 በመቶ በላይ የዞኑ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ ማቋረጣቸውን ፓርቲው ጨምሮ ገልጧል፡፡

3፤ በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን 59 ሺህ በላይ መሻገሩን የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በላከለት መግለጫ መግለጡን ሸገር ዘግቧል። ኮሚሽኑ፣ ባለፈው አንድ ወር ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡና የሱዳናዊያን ስደተኞች ብዛት ብቻ ከ52 ሺህ 600 በላይ መድረሱን ኮሚሽኑ መጥቀሱን ዘገባው አመልክቷል፡፡ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ 426 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል መባሉንም ዜና ምንጩ ጠቅሷል፡፡

4፤ አሜሪካ፣ ለምታሰለጥነው የሱማሊያው ልዩ ኮማንዶ "ዳናብ" የምትሰጠውን የምግብ ድጋፍ ልታቋርጥ መሆኑን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። አሜሪካ የምግብ ድጋፏን ለማቋረጥ የወሰነችው፣ ልዩ ኮማንዶው የምግብና የነዳጅ ድጋፉን መልሶ ገበያ ውስጥ በመሸጥ በሙስና ተዘፍቋል የሚል መረጃ ከደረሳት በኋላ እንደኾነ ዘገባዎቹ ገልጸዋል። አሜሪካ ለልዩ ኮማንዶው የምታቀርበውን የነዳጅ ድጋፍ ጭምር ልታቋርጥ እንደምትችል ምንጮች ተናግረዋል ተብሏል። "ዳናብ" ልዩ ኮማንዶ አልሸባብን በመውጋት እውቅናን ያተረፈ የጦር ሠራዊቱ ክፍል ነው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ ሚያዝያ 17/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ሚንስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በወጪ ንግድ ላይ የቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት የሚደነግግ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ አጽድቋል። ምክር ቤቱ፣ የወጪ ንግድ ቀረጥ ላይ ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ላይ ቀረጥ እንዲቀንስ የወሰነው፣ ለአገሪቱ ኢንደስትሪ ልማትና ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ፣ በወጪ ንግድ መስክ የተሠማሩ ባለሃብቶችና ኩባንያዎችን ለማበረታታት እንዲኹም የወጪ ንግዱን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደኾነ ገልጧል። መንግሥት በዘርፉ ላይ የቀረጥ ማሻሻያ ያደረገው፣ የውጭ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ከነዳጅ እና ማዳበሪያ ውጭ ባሉ ሸቀጦች በጅምላ እና ችርቻሮ የወጪና ገቢ ንግድ እንዲሠማሩ በፈቀደ ማግስት ነው።

2፤ የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋም ኮሚሽን የትግራይ ኃይሎችን በሰኔ ወር ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተንና መልሶ የማዋሃድ ሂደት እንደሚያከናውን መግለጡን በኢትዮጵያ የካናዳ ኢምባሲ አስታውቋል። ኮሚሽኑ ይህን የገለጠው፣ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላኹን ባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ከኾኑት ጆሹዋ ታባህ ጋር በተወያዩበት ወቅት እንደኾነ ኢምባሲው ባሠራጨው መረጃ ገልጧል። ብሄራዊ የደኅንነት ምክር ቤት፣ የሕወሃት ኃይሎች በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት ትጥቅ መፍታት አለባቸው ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ ማሳሰቡ ይታወሳል። 

3፤ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የንግድ ማነቆዎችን ለማስወገድ አዲስ ጥረት እንደጀመሩ ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። አዲሱ ጥረት የተገለጠው፣ የኬንያና ኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቡድን ሰሞኑን በአዲስ አበባ የጋራ ስብሰባውን ባደረገበት ወቅት ነው። በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2022 ኬንያ 95 ሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ሸቀጦችን ወደ ኢትዮጵያ የላከች ሲኾን፣ ኢትዮጵያ ጥራጥሬና አትክልቶችን ጨምሮ በተጠቀሰው ዓመት ወደ ኬንያ የላከችው ግን 26 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። በኹለቱ አገሮች ድንበር ዘለል ንግድ ውስጥ ሊወገዱ ከሚገባቸው ማነቆዎች መካከል፣ ታሪፍ ነክ ያልሆኑ ማነቆዎችና ባንዱ አገር ጥራቱ የተረጋገጠለት ምርት በሌላኛው አገር በድጋሚ ጥራቱ እንዲረጋገጥ የማድረግ አሠራር እንደሚገኙበት ዘገባው ጠቅሷል።

4፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአምስት ዓመታት በፊት በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላን ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ወገኖች ትናንት ከአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት፣ የተጎጂዎቹ ቤተሰቦች ባለሥልጣናቱ በቦይንግ ኩባንያ ስህተት ለደረሰው አደጋ በኩባንያው ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሠርቱ ጠይቀዋል። ባለሥልጣናቱ በበኩላቸው፣ በኩባንያው ላይ ክስ የመመስረቱን ጉዳይ ገና እያጤኑት እንደኾነ ለተጎጂዎች ቤተሰቦች ነግረዋቸዋል። የተጎጂዎች ቤተሰቦች ግን ፍትህ መስሪያ ቤቱ ክሱን ለመመስረት ቁርጥ ያለ አቋም ላይ አለመድረሱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። ቦይንግ በማክስ አውሮፕላን ላይ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ከፍትህ ሚንስቴር ዓቃቤ ሕግ ጋር ከሦስት ዓመት በፊት ውል ገብቶ የነበረ ቢኾንም፣ የአላስካ አየር መንገድ ንብረት የኾነ ማክስ አውሮፕላን ከጥቂት ሳምንታት በፊት በረራ ላይ እያለ በሩ መገንጠሉ የክሱን ጉዳይ እንደገና ቀስቅሶታል።

5፤ "ቴላቪቭ" የተሰኘ ጽሁፍ የተጻፈበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የመንገደኞች አውሮፕላን ለእስራኤል እውቅና ከማትሰጠው ሊባኖስ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፉን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኾኖም አውሮፕላኑ የቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያን እንዳረፈ፣ የአገሪቱ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣናት አውሮፕላኑ "ቴላቪቭ" የሚለውን ጽሁፍ ባስቸኳይ እንዲሸፍን ማድረጋቸውና አውሮፕላኑ ጽሁፉን እንደሸፈነ ከቤይሩት አየር ማረፊያ እንደቀቀ ተገልጧል። የሊባኖስ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሊባኖስ ወደፊት በረራዎችን ሲያደርግ፣ ከእስራኤል ጋር የተገናኙ ምልክቶችን እንዳይጠቀም እንዳሳሰበ ተነግሯል። አየር መንገዱ በበኩሉ፣ አዲስ በተገዛ አውሮፕላን አካል ላይ አውሮፕላኑ መጀመሪያ ያረፈበትን የአውሮፕላን ማረፊያ ስም መጻፍ የተለመደ አሠራር መኾኑን ገልጧል ተብሏል። እስራኤል፣ ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ የሂዝቦላ ዒላማዎችን ለመምታት በሚል ሊባኖስ ውስጥ ተደጋጋሚ የአውሮፕላን ጥቃቶችን እንደምትፈጽም ይታወቃል።

6፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ የአንቶኒዮ ጉተሬዝ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ራማታን ላማምራ፣ የሱዳኑን ጦርነት ማስቆም በሚችልበት ኹኔታ ዙሪያ ለመምከር በቀጠናው አገሮች ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። ልዩ መልዕክተኛው ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ አቅንተው በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረው ነበር። ላማማራ ዛሬ ደሞ ወደ አሥመራ አቅንተው፣ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በሱዳኑ ጦርነት ዙሪያ ተወያይተዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ የሱዳኑ ጦርነት እስካኹን መፍትሄ ያጣው፣ የሰላም ጥረቶች በመብዛታቸውና ወጥ የኾነ የሰላም ጥረት ባለመኖሩ እንደኾነ ለላማማራ እንደገለጡላቸው የኤርትራ ቃል አቀባይ የማነ ገብረ መስቀል በ"ኤክስ" ገጻቸው ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ የተመድ ዋና ጸሃፊ በጎረቤት አገራት በኩል ወደ ሱዳን የሚገባውን ጦር መሳሪያ ለማስቆም የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን የማነ ጠቅሰዋል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ8795 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ0171 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ5577 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ9089 ሳንቲም ኾኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ7928 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ0087 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ሚያዝያ 17/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢትዮ ቴሌኮም አዲስ አበባን ጨምሮ በ29 ከተሞች ብሄራዊ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ መጀመሩን አስታውቋል። ኩባንያው በወር በአማካይ 1 ሚሊዮን ዜጎችን ለመመዝገብና ባጠቃላይ መታወቂያውን ለ32 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ እንዲኾን ለማድረግ ማቀዱን ገልጧል። ኩባንያው፣ አገልግሎቱን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በሌሎች ከተሞች ጭምር ማስፋፊያ አከናውናለኹ ብሏል፡፡ ብሄራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት፣ የዲጂታል መታወቂያን እስከ 2018 ዓ፣ም ድረስ ለ90 ሚሊዮን ዜጎች ለማዳረስ አቅዷል።

2፤ የፌደራል መንገዶች አስተዳደር፣ በጸጥታ ችግር ሳቢያ በተስተጓጎሉ የመንገዶች ግንባታ ተቋራጮች ከ34 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ እንደጠየቁት ትናንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ መናገሩን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። አስተዳደሩ እስከ በጀት ዓመቱ አጋማሽ ድረስ 31 የመንገድ ፕሮጀክቶች በጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ የግንባታ ውላቸው እንደተቋረጠ መግለጡን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። በቀጣዩ በጀት ዓመት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደማይጀመሩ ተገልጧል።

3፤ መንግሥት ያቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ፣ ትናንት በሦስት በረራዎች ከሳዑዲ ዓረቢያ ባስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የነበሩ 1 ሺህ 181 ዜጎችን ወደ አገራቸው መልሷል። ከተመላሾቹ መካከል፣ አራቱ ታዳጊዎች እንደኾኑ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጧል። ብሄራዊ ኮሚቴው ዜጎችን ከሳዑዲ ዓረቢያ መመለስ የጀመረው ከሚያዚያ 4 ጀምሮ ሲኾን፣ ባጠቃላይ ለመመለስ ካሰባቸው 70 ሺህ ፍልሰተኞች ውስጥ እስካኹን ከ9 ሺህ በላይ የሚኾኑትን እንደመለሰ ሚንስቴሩ ገልጧል።

4፤ ሰርቢያ የሚገኘው የሱማሊያ ኢምባሲ፣ የኢትዮጵያውን ኦጋዴን፣ ጅቡቲንና የሰሜን ኬንያ ግዛትን ያካተተ ካርታ በ"ኤክስ" (በቀድሞው ትዊተር) ገጹ አሠራጭቷል። ኢምባሲው፣ ካርታው "የታላቋ ሱማሊያ" ካርታ መኾኑን ገልጧል። "የታላቋ ሱማሊያ" ካርታ፣ የቀድሞው የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ ጀኔራል ዚያድ ባሬ ያራምዱት የነበረው የተስፋፊዋ ሱማሊያ ካርታ እንደኾነ ይታወቃል። የዚያድ ባሬ መንግሥት በዚኹ ኦፊሴላዊ የተስፋፊነት ፖሊሲው ሳቢያ፣ የኦጋዴን ግዛትን ለመጠቅለል ወረራ ፈጽሞ እንደነበር አይዘነጋም። የሱማሊያ መንግሥት፣ ኢምባሲው ባሠራጨው "የታላቋ ሱማሊያ" ካርታ ዙሪያ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ማስተባበያ አልሰጠም። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ረቡዕ ሚያዝያ 16/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የብሄራዊ ደኅንነት ምክር ቤት፣ በግጭት ማቆም ስምምነቱ መሠረት የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት እንዳለባቸው ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ምክር ቤቱ፣ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ጉዳይም ቀደም ሲል በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትም ገልጧል። ምክር ቤቱ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን የሚያግቱና የሚዘርፉ ቡድኖችን መሸከም ሊያበቃ እንደሚገባውም ምክር ቤቱ አሳስቧል።

2፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ቢሮ፣ መንግሥት ከሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ውጪ በሚንቀሳቀሱ በርካታ የጸጥታ አካላት ላይ ርምጃ መውሰዱን ሪፖርተር ዘግቧል። የከተማዋ አንዳንድ የጸጥታ አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ሕገወጥ እስራቶችን ስለመፈጸማቸው ቢሮው መግለጡን ዘገባው አመልክቷል። ቢሮው፣ በጸጥታ አካላቱ ድርጊቶች ላይ ግምገማና ክትትል በማድረግ፣ ከእስራት ጀምሮ ከሥራ እስከ ማሰናበት የሚደርሱ ርምጃዎችን መውሰዱ ተገልጧል። ለሥራ ፍለጋ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ወደ ከተማዋ የሚደረገው ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መኾኑን የጠቀሰው ቢሮው፣ ከፍልሰተኞች ውስጥም ጸጥታ የማደፍረስ ተልዕኮ ይዘው የሚገቡ መኖራቸውንና ቢሮው አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸውን ለመለየትና ለመቆጣጠር ጥረት እያደረኩ ነው ማለቱን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

3፤ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ ሊኾኑ የሚችሉ ጉዳዮችን እንዲያዘጋጁ በደብዳቤ መጠየቁን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። ኮሚሽኑ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚመርጧቸው አጀንዳዎች ዙሪያ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እንዲያደርጉ መድረኮችን እንደሚፈጥር መግለጡን ዘገባው አመልክቷል። ኮሚሽኑ የምክክር አጀንዳዎችን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚጀምር በቅርቡ ገልጦ ነበር።

4፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የኾኑትን ቀሲስ በላይ መኮንንን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ 8 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን የአገር ውስጥ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። የቀሲስ በላይ መኮንን እና ተጠርጣሪ ግብረ አበሮቻቸው ጠበቆች፣ ፖሊስ ዋስትና ለማስከልከል ያቀረባቸው ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም በማለት ተከራክረው እንደነበር ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ፖሊስ ካኹን ቀደም በተሰጠው የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ፣ በወቅቱ የነበረ የካሜራ ቅጂ ከአፍሪካ ኅብረት መጠየቁን፣ ለወንጀል ተግባር የዋለ ተሽከርካሪ ማረጋገጫ ለማግኘት ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ማቅረቡን፣ በተጠርጣሪው ኹለት መኖሪያ ቤቶች ላይ ብርበራ ማድረጉንና በብርበራ የተገኘ አንድ የጦር መሳሪያ ሕጋዊነቱን የማረጋገጥ ሥራ እየሰራ መኾኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል ተብሏል። ቀሲስ በላይ ከሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት፣ ከአፍሪካ ኅብረት የባንክ አካውንት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በሐሰተኛ ሰነዶች ለማውጣት ሞክረዋል ተብለው ተጠርጥረው እንደኾነ አይዘነጋም።

5፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ8613 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ9985 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ0745 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ4160 ሳንቲም ኾኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ6028 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ8149 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ ሚያዝያ 16/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በጅቡቲ የባሕር ጠረፍ ላይ በጀልባ መገልበጥ የሞቱ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ብዛት 21 መድረሱን ሮይተርስ ዓለማቀፉን የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ጠቅሶ ዘግቧል። ከጀልባዋ 77 ተሳፋሪዎች መካከል፣ 23ቱ ፍልሰተኞች እስከ ትናንት ምሽት ድረስ የደረሱበት እንዳልታወቀ ዘገባው ጠቅሷል። ከአደጋው የተረፉት 33 ፍልሰተኞችና በአደጋው የሞቱት ፍልሰተኞች ኹሉም ኢትዮጵያዊያን እንደኾኑ በጅቡቲ የድርጅቱ ሃላፊዎች አረጋግጠዋል ተብሏል።

2፤ የትግራዩ ተቃዋሚ ሳልሳዊ ወያነ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሰባት አገራት ኢምባሲዎች የትግራይን ግዛቶች "አወዛጋቢ ቦታዎች" በሚል ቃል መግለጣቸውን ኮንኗል። ፓርቲው፣ "አወዛጋቢ" የተባሉት አካባቢዎች "በኃይል የተያዙ የትግራይ ግዛቶች እንጅ ውዝግብ የተነሳባቸው አይደሉም" ብሏል። ኢምባሲዎቹ የትግራይ ግዛቶችን በኃይል የያዙ ኃይሎች በመውጣታቸው አስፈላጊነት ላይ አጽንዖት እንዲያደርጉ ፓርቲው ጠይቋል። የአሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ጃፓን ኢምባሲዎች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ "ውዝግብ ባለባቸው አካባቢዎች" የተፈጠረው አዲስ ውጥረት እንዳሳሰባቸው ቅዳሜ'ለት ባወጡት መግለጫ መግለጣቸው አይዘነጋም።

3፤ በኢትዮጵያ የገዳዩን ካላዛር በሽታ ለማጥፋት ኹለተኛ ዙር የአዲስ መድሃኒት ሙከራ በጎንደር ዩኒቨርስቲ አማካኝነት እየተካሄደ እንደኾነ ተሰምቷል። በትንኝ አማካኝነት የሚተላለፈው ካላዛር፣ በዓለም ከወባ ቀጥሎ በገዳይነቱ ኹለተኛው በሽታ ነው። እስካኹን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ሕክምና፣ ለ17 ተከታታይ ቀናት ሆስፒታል ውስጥ ብቻ በመርፌ የሚሰጥና ተጓዳኝ ሕመሞችን የሚያስከትል መድሃኒት እንደኾነ ይታወቃል። ባንጻሩ አኹን ኢትዮጵያ ውስጥ በሙከራ ላይ ያለው መድሃኒት፣ በጤና ጣቢያዎች ውስጥ በአፍ አማካኝነት በቀላሉ የሚሰጥ ክኒን እንደኾነ ተነግሯል።

4፤ የሱማሊያ መከላከያ ሚንስትር አብዱልቃድር ሞሃመድ ኑር፣ ተጨማሪ የቱርክ የባሕር ኃይል የጦር መርከቦች ወደ ሱማሊያ የባሕር ጠረፍ እየመጡ መኾኑን መናገራቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የመጀመሪያዋ የቱርክ የባሕር ኃይል የጦር መርከብ ትናንት ሞቃዲሾ ወደብ ደርሳለች። ቱርክ ከሱማሊያ ጋር በተፈራረመችው የባሕር ኃይል ስምምነት መሠረት፣ የቱርክ ባሕር ኃይል ለሱማሊያ ባሕር ኃይል ሥልጠና እንደሚሰጥና የአገሪቱን የባሕር ወሰን ከባሕር ላይ ወንበዴዎች፣ ከአሸባሪዎች፣ ከሕገወጥ አሳ አስጋሪዎችና ከውጭ ጣልቃ ገብነት እንደሚከላከል ይጠበቃል። ቱርክ ምን ያህል የባሕር ኃይል ወታደራዊ መርከቦችን በሱማሊያ የባሕር ወሰን እንደምታሠማራ አልተገለጠም።

5፤ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ፣ ብሪታኒያ ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያጸደቀችውን አዲስ ሕግ እንደገና እንድታጤነው ጠይቀዋል። አዲሱ ሕግ ዓለማቀፍ ሰብዓዊ መብቶችን ይሸረሽራል ያሉት ኮሚሽነሮቹ፣ ብሪታንያ ለኢመደበኛ ፍልሰትና ስደት ሌሎች አማራጭ መፍትሄዎችን እንድትፈልግ ጠይቀዋል። ብሪታንያ በአዲሱ ሕጓ ከ10 እስከ 12 ሳምንታት ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ወደ ግዛቷ የገቡ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ትልካለች። የአገሪቱ መንግሥት ለወራት ሲጓተት የቆየውን እቅዱን እንደሚተገብር የገለጸው፣ የላይኛውና የታችኛው ፓርላማዎች አዲሱን ሕግ ማጽደቃቸውን ተከትሎ ነው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ ሚያዝያ 15/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ሕወሓት ገዥውን ፓርቲ ብልጽግናን ለመቀላቀል ከፓርቲው ጋር ተከታታይ ድርድሮች እያደረገ እንደሚገኝ ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች። ኾኖም ሕወሓት የብልጽግና ፓርቲ ሕገ-ደንብ እንዲሻሻልና የፓርቲው አባል የሚኾኑ ድርጅቶች እኩል የማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈጻሚ አባላት ውክልና እንዲኖራቸው ቅድመ ኹኔታ ማቅረቡ ታውቋል። ብልጽግና በበኩሉ፣ ሕወሓት እንደ ድርጅት ራሱን አክስሞ ውህዱን ፓርቲ እንዲቀላቀልና ውክልናውም በገዥው ፓርቲ ሕገ ደንብ መሠረት በትግራይ ሕዝብ ቁጥር ልክ እንዲወሰን ይፈልጋል። በአዲስ አበባ ተገኝተው ከገዥው ፓርቲ ጋር ድርድሩን የጀመሩት የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረ ሚካዔል ናቸው። በሕወሃትና በገዥው ፓርቲ መካከል ድርድር እየተደረገ መኾኑ የተሰማው፣ ምርጫ ቦርድ የሕወሃትን ሕጋዊ ሰውነት የሰረዘበትን ውሳኔ ባልሻረበት ኹኔታ ነው። Link- https://tinyurl.com/4becc7ya

2፤ ሕወሃት፣ በውህደት ዙሪያ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ውይይት እያደረገ ስለመኾኑ የተሠራጨው ዘገባ "ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው" በማለት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስተባብሏል። ሕወሃት፣ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ባኹኑ ወቅት እያደረገው ያለው ንግግር፣ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት የሰፈነውን ሰላም በማስፋትና በማጠናከር ዙሪያ ብቻ እንደኾነ ገልጧል። በሕወሃትና በገዥው ፓርቲ መካከል በርዕዮተ ዓለም እና በዓላማ ረገድ መሠረታዊ ልዩነቶች እንዳሉ የገለጠው የሕወሃት መግለጫ፣ ኾኖም ኹለቱ ፓርቲዎች የሚወያዩባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ ብሏል። ዋዜማ፣ በሕወሃትና በብልጽግና ፓርቲ መካከል በውህደት ዙሪያ ንግግሮች እንደተጀመሩ ዛሬ ጧት መዘገቧ አይዘነጋም።

3፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ በራያ አካባቢ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተፈጠረው ውጥረት ሳቢያ ከአላማጣ አካባቢ ወደ ቆቦ እና ሰቆጣ የተፈናቀለው ሕዝብ ከ50 ሺህ በላይ መድረሱን አስታውቋል። 42 ሺህ ተፈናቃዮች ቆቦ ከተማ እንዲኹም 8 ሺህ 300 ተፈናቃዮች ሰቆጣ እንደገቡና አብዛኞቹ ሴቶችና ሕጻናት እንደሆኑ ቢሮው ገልጧል። በአላማጣ እና ቆቦ መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት እንደቀጠለ መኾኑና የጠቀሰው ቢሮው፣ በቅርቡም በአላማጣና ማይጨው ከተሞች መካከል የትራንስፖርት አገልግሎት እንደገና እንደተጀመረ ገልጧል። ኾኖም ከወልድያ ወደ ሰቆጣ የሚወስደው መንገድ ደኅንነቱ አስተማማኝ ባለመኾኑ፣ ወደ ሰቆጣ የሄዱ ተፈናቃዮች እስካሁን ለረድዔት ድርጅቶች ተደራሽ አይደሉም ተብሏል። ቢሮው፣ ለአዲሶቹ ተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ ለረድዔት ድርጅቶች ጥያቄ ማቅረቡንም ጠቅሷል።

4፤ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ አጎና በተባለች አነስተኛ ከተማ ባለፈው ሰኞ በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ተከትሎ አምስት ንጹሃን እንደተገደሉ ቢቢሲ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል። ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ኃይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ጥቃቱን እንደፈጸሙ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። የመንግሥት ኃይሎች ግድያውን የፈጸሙት፣ የፋኖ ታጣቂዎችን ትደግፋላችኹ በማለት እንደኾነ ነዋሪዎች ተናግረዋል ተብሏል። ዘገባው፣ በጥቃቱ በርካታ መኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉ መስማቱንም ጠቅሷል።

5፤ ዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም)፣ ትናንት ቀይ ባሕር ላይ ባጋጠመ የጀልባ መገልበጥ አደጋ 16 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን እንዳለፈ አስታውቋል። ድርጅቱ፣ 28 ኢትዮጵያዊያን የጀልባዋ ተሳፋሪዎች ደሞ እስካኹን የደረሱበት እንዳልታወቀ ገልጧል። አደጋው የደረሰው፣ ከየመን የባሕር ዳርቻ 77 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን በመጫን ወደ ጅቡቲ ስትጓዝ በነበረች ጀልባ ላይ እንደኾነ ተገልጧል። ከሟቾቹ መካከል፣ 5 ሕጻናት እና ሴቶች እንደሚገኙበትና 33 ፍልሰተኞች ከአደጋው በሕይወት እእንደተረፉ ድርጅቱ ባሠራጨው መረጃ አመልክቷል።

6፤ ቱርክ፣ የባሕር ኃይል የጦር መርከቧን ወደ ሱማሊያ የባሕር ጠረፍ መላኳን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የቱርክ የጦር መርከብ ዛሬ ከሱማሊያ የባሕር ጠረፍ የደረሰችው፣ ኹለቱ አገራት ከጥቂት ወራት በፊት በተስማሙት የባሕር ኃይል ስምምነት መሠረት ነው። ኢትዮጵያ ከሰሜን ሶማሊላንድ ራስ ገዝ የባሕር ኃይል ጣቢያ መገንቢያ ቦታ ለማግኘት የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመች ማግስት፣ ሱማሊያና ቱርክ የኹለትዮሽ የባሕር ኃይል ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። የኹለትዮሽ ስምምነቱ፣ ቱርክ ለሱማሊያ የባሕር ጠረፍ ወታደራዊ ጥበቃ እንድታደርግ የሚፈቅድ ነው። ከዚኹ ስምምነት ጋር በተያያዘ፣ ቱርክ በሱማሊያ የውቅያኖስ ዳርቻ የተፈጥሮ ጋዝ ቁፋሮ ልትጀምር እንደኾነ ተሰምቷል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ8499 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ9869 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 66 ብር ከ8819 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ2195 ሳንቲም ኾኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ5167 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ7270 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ ሚያዝያ 15/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ አብን፣ ፌደራል መንግሥቱ የሕወሃት ታጣቂዎችን ሰሞኑን ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ባስቸኳይ እንዲያስወጣና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። አብን፣ ሕወሃት በአማራ ሕዝብ ላይ ሌላ ዙር የጦርነት ጉሰማ ሲጀምር መንግሥት የሚያሳየው የሃላፊነትና የግልጽነት ጉድለት አገሪቱ ወደባሰ ችግር ውስጥ እንድትገባ ግንባር ቀደም አስተዋጽዖ አድርጓል በማለት ከሷል። አብን አያይዞም፣ የሕወሃት ታጣቂዎች በራያ ባላ፣ አላማጣና ኦፍላ ወረዳዎች እና በኮረም ከተማ የሕዝብ፣ የመንግሥትና የሃይማኖት ተቋማትንና የነዋሪዎችን ንብረት ዘርፈዋል ብሏል።

2፤ ኢሠማኮ፣ ዘንድሮ ሚያዝያ 23 ቀን በኢትዮጵያ ለ49ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም ሠራተኞች ቀን በአዳራሽ ውስጥ ብቼ እንዲከበር መወሰኑን አስታውቋል። ኢሠማኮ፣ በበዓሉ የአከባበር ሁኔታ ላይ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፣ "የአገሪቱን አጠቃላይ ኹኔታ" እና "በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ" ሥር የሚገኙ አከባቢዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደኾነ ገልጧል። ኾኖም ይህ የበዓሉ አከባበር፣ ባሕርዳር፣ ኮምቦልቻና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችን እንደማይጨምር ኢሠመኮ አመልክቷል። የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት፣ እስከ በዓሉ ድረስ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሠራተኞችን ተወካዮች በሠራተኛው ጥያቄዎች ዙሪያ እንዲያነጋግሩ መወሰኑንና ጥያቄው ለጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት መቅረቡን ኢሠማኮ ጨምሮ ገልጧል።

3፤ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ትናንት ናይጀሪያ ውስጥ ባካሄዱት ጉባዔ፣ ነውጠኛ ጽንፈኝነትን ለመዋጋት የአሕጉሪቱ ተቋማት ይበልጥ እንዲጠናከሩ ጥሪ አድርገዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ፣ በአሕጉሪቱ ውስጥ በየቀኑ የሚፈጸሙ የጽንፈኞች ጥቃቶች ካለፉት ኹለት ዓመታት ወዲህ ከአራት ወደ ስምንት መጨመራቸውን በጉባዔው ላይ ተናግረዋል። ፋኪ፣ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በጽንፈኞች ጥቃት፣ በአሕጉሪቱ 7 ሺህ ሲቪሎችና 4 ሺህ ወታደሮች መገደላቸውን ጠቅሰዋል።

4፤ የዓለም ጤና ድርጅት፣ "ቤኒሊን" የተሰኘው መርዛማ ንጥረ ነገር የተገኘበት የሕጻናት ሲረፕ መድሃኒት ባሁኑ ወቅት በአፍሪካ አገራት ውስጥ እንደማይገኝ ማረጋገጡን አስታውቋል። በተያዘው ወር፣ ኬንያ፣ ናይጀሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌና ደቡብ አፍሪካ መድሃኒቱን አስወግደዋል። ይህንኑ ተከትሎ ድርጅት፣ በመድሃኒቱ ዙሪያ ሊያወጣው የነበረውን ዓለማቀፍ "የጤና አደጋ ማስጠንቀቂያ" መሰረዙን ገልጧል። በመድሃኒቱ ውስጥ የተገኘው መርዛማ ንጥረ ነገር፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጋምቢያ፣ ካሚሮን፣ ኢንዶኔዥያና ኡዝቤኪስታን ከ300 በላይ ሕጻናት እንዲሞቱ ምክንያት ኾኗል። [ዋዜማ]
#NewsAlert
ሕወሓት ከአራት ዓመት በፊት “ሕገ – ወጥ ነው” ያለውን ገዥውን ፓርቲ ብልፅግና ለመቀላቀል ተከታታይ ድርድሮች እያደረገ መሆኑን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል። ዝርዝሩን ያንብቡት https://tinyurl.com/4becc7ya
ለቸኮለ! ሰኞ ሚያዝያ 14/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ ከአማራ ክልል በተነሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ባለፈው ሳምንት ዓርብ በርካታ ሰዎችን አፍኖ መውሰዱን ዋዜማ በስፍራው ካሉ ምንጮቿ ሰምታለች። አማጺው ቡድን እገታውን የፈጸመው፣ በጎሃጽዮን እና ቱሉ ሚልኪ ከተሞች መሃል ባለች ቢቱ ወንዝ ተብላ በምትጠራ ሥፍራ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል። እገታው የተፈጸመው፣ መነሻውን ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ባደረገው በተልምዶ "ታታ" ተብሎ በሚጠራ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ እና በሦስት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ሲጓዙ በነበሩ መንገደኞች ላይ እንደኾነ ምንጮች ጠቁመዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፣ ታፍነው የተወሰዱት ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ስር መኾናቸውንም ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት መረዳት ችላለች።

2፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ ለኮሪደር ልማት ሲል ያፈረሳቸውን ሠፈሮች ጨምሮ በ250 በላይ ቦታዎች ላይ የሊዝ ጨረታ ማውጣቱን ዋዜማ ተረድታለች። የሊዝ ጨረታው የወጣባቸው ቦታዎች በአስር ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ናቸው። በፈረሰው ፒያሳ አካባቢ 2 ሺህ 179 ካሬ ሜትር ስፋት ካለው ቦታ ጀምሮ እስከ ዝቅተኛው 650 ካሬ ሜትር ድረስ የሚገኙ 22 ቦታዎች የሊዝ ጨረታ ወጥቶባቸዋል። አስተዳደሩ ለ22ቱም ቦታዎች ያቀረበው የሊዝ መነሻ ዋጋ በካሬ 2 ሺህ 213 ብር ከ25 ሳንቲም ነው። የአኹኑ የሊዝ ጨረታ፣ የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ካወጣው የሊዝ ጨረታ በኋላ ለኹለተኛ ጊዜ የወጣ ነው።

3፤ አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጃፓን እና ጣሊያን፣ የትግራይ እና አማራ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ሰሞኑን የተፈጠረው ውጥረት እንዳሳሰባቸው ሰሞኑን በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ኹሉም ወገኖች የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ መበተን እና መልሶ ማዋሃድ ሂደቱ እንዲተገበርና ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ጥረት ማድረጋቸው አስፈላጊ መሆኑን አገራቱ ጠቅሰዋል። አገራቱ፣ አዲስ አበባ በሚገኙ ኢምባሲዎቻቸው በኩል ባወጡት በዚኹ መግለጫ፣ ሰሞኑን ባንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ እና ሰላማዊ ሰዎች ከጥቃት እንዲጠበቁም ጥሪ አድርገዋል። የኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካና ጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ በኹሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ኹሉን አካታች ንግግር እንዲኖር ማድረግ ብቸኛው መፍትሄ እንደኾነም ኢምባሲዎቹ ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፣ ከራያ አላማጣ ወረዳ አላማጣ ከተማ በውጥረቱ ሳቢያ ከ29 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ቆቦ እና ሰቆጣ መፈናቀላቸውን መግለጡ አይዘነጋም።

4፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን፣ ጎርካ ወረዳ ታጣቂዎች ትናንት አራት ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ዶይቸቨለ ዘግቧል። በጎርካ ወረዳ ቆቦ በተባለ ቀበሌ ግድያውን የፈጸሙት፣ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላን ወረዳ የተነሱ ታጣቂዎች እንደኾኑ የአካባቢው ነዋሪዎች መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሬ ሕዝብ ተወካይ አወቀ ሃምዛዬ፣ መንግሥት ባካባቢው መከላከያ ሠራዊት እንዲያሠፍር ካሁን ቀደም ተጠይቆ ምላሽ እንዳልሰጠ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ከጉጂ የሚነሱ ታጣቂዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኮሬ ዞን በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለው በርካቶችን ከቀያቸው ማፈናቀላቸው ሲነገር ቆይቷል። ባለፈው ጥር ወር ብቻ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች፣ በዞኑ ገላን ወረዳ ውስጥ 12 የክልሉን ሚሊሺያ አባላት እንደገደሉ እንደተዘገበ አይዘነጋም።

5፤ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው ሰደድ እሳት እስካኹን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር እንዳልዋለ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር መናገሩን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። ሰደድ እሳቱን በማስነሳት የተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉና የእሳት ቃጠሎውን መንስዔ ለማወቅ የማጣራት ሂደት እንደተጀመረ አስተዳደሩ መግለጡን ዘገባው አመልክቷል። ባለፉት ቀናት በቃጠሎው ጉዳት የደረሰበት አካባቢ ብርቅዬዎቹ ቀበሮ እና ዋልያ አይቤክስ የሚገኙባቸውና በጓሳ ሳር የተሸፈኑ አካባቢዎች እንደኾኑ ሃላፊዎች ተናግረዋል ተብሏል።

6፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ8323 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ9689 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ6047 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ9568 ሳንቲም ኾኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ6230 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ8355 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ ሚያዝያ 14/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ቀንዓ ያደታን ምክትል የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው አድርገው እንደሾሙ ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። ቀንዓ፣ ቀደም ሲል የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ፣ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር እንዲኹም መከላከያ ሚንስትር ኾነው አገልግለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው በነበሩትና የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኾነው በተሾሙት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ምትክ፣ እስካኹን ሌላ ዋና የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ አልሾሙም።

2፤ የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት በጆር ወረዳ ባለፈው መጋቢት ወር በተፈጸመ ጥቃት ሃላፊነታቸውን ባግባቡ ያልተወጡ ሰባት የዞን እና የወረዳ ሃላፊዎችን ከሥልጣን ማባረሩንና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን ትናንት አስታውቋል። ከሥልጣን ተነስተው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሃላፊዎች፣ በጥቃቱ ወቅት የክልሉ መንግሥት መረጃዎች እንዳይደርሱት የደበቁ ናቸው ብሏል። መጋቢት 26 ቀን ከደቡብ ሱዳን የተነሱ ታጣቂዎች በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር በመቀናጀት በጆር ወረዳ ፈጸሙት በተባለው ጥቃት፣ 730 መኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉ፣ ሰባት ሕጻናት ተጠልፈው እንደተወሰዱ፣ በርካታ የቤት እንስሳት እንደተዘረፉና ስድስት ሺህ ነዋሪዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ የክልሉ መንግሥት ገልጧል።

3፤ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን፣ በሰሜኑ ጦርነት ለተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ያቀረበውን የልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም አስፈላጊነት መንግሥት ውድቅ እንዳደረገው ከምንጮች መስማቱን ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል። የሚንስትሮች ምክር ቤት፣ የቡድኑን ምክረ ሃሳብ ውድቅ ያደረገው ባለፈው ሳምንት ረቂቅ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲውን ባጸደቀበት ስብሰባው ላይ ነው። የሚንስትሮች ምክር ቤት፣ ከባድ ወንጀሎች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ሥር በሚቋቋሙ ልዩ ችሎቶች እንዲታዩ መወሰኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ኾኖም፣ ለከባድ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራዎች የክስ ሂደቶች ልዩ ነጻና ገለልተኛ ዓቃቤ ሕግ እንዲኹም እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን እንዲቋቋም ቡድኑ ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ፣ መንግሥት እንደተቀበለው ዘገባው ጠቅሷል።

4፤ የሶማሌላንድ ራስ ገዝ መንግሥት፣ የቡድን-7 አገራት የሶማሌላንድና ኢትዮጵያን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት አስመልክተው ባወጡት መግለጫ፣ "ሶማሌላንድን የሱማሊያ ግዛት አድርገው መጥቀሳቸው አስቆጥቶኛል" ብሏል። የቡድን-7 አገራት፣ ሶማሊላንድ ራሷን የቻለች አገር የኾነችበትን ታሪካዊ ዳራና ነባራዊ ሃቅ ሊስቱት እንደማይገባ የራስ ገዟ መንግሥት አውስቷል። የሱማሊያ መንግሥት ሊቋቋማቸው የማይችላቸውን ታሪካዊ ግጭቶች እንደገና ለመቀስቀስ ጥረት እያደረገ መኾኑንም፣ የቡድን-7 አገራት ማወቅ አለባቸው ሲል የሶማሊላንድ መንግሥት አሳስቧል። የቡድን-7 አገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች፣ ሶማሊላንድን የሱማሊያ ግዛት አድርገው የጠቀሱት ሱማሊያና ኢትዮጵያ በባሕር በር ዙሪያ ለገቡበት ውዝግብ የንግግር መስመሮችን ክፍት እንዲያደርጉ በጠየቁበት የዓርብ'ለቱ መግለጫቸው ላይ ነበር። [ዋዜማ]
ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ለህዝብ ይፋ የተደረገ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አላቀረበችም። ይሁንና ከነባሩ ፖሊሲ ብዙ የተቀየሩ ጉዳዮች እንዳሉ ከመንግስት ድርጊቶችና አስተያየቶች መረዳት ይቻላል። በጉዳዩ ላይ እንግዶች ጋብዘናል። የዋዜማን ከስምንተኛ ወለል የስቱዲዮ ውይይት ሁለተኛ ክፍል ጋብዘናችኋል - https://tinyurl.com/488wx94x
#wazemaradio#lechekole#ethiopia#Wazema
በፒያሳ ለኮሪደር ልማት የፈረሱ ሰፈሮችን ጨምሮ በከተማው በርካታ ቦታዎች የሊዝ ጨረታ ወጣ- ዝርዝሩን ያንብቡት- https://tinyurl.com/yxymdduj
#NewsAlert
የቀድሞ የመከላከያ ሚንስትር ቀንዓ ያደታ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ምክትል የደህንነት አማካሪ ሆነው ተሾሙ። ዋዜማ በደረሳት መረጃ መሰረት ቀንዓ ያደታ በሚንስትር ዴዔታ ማዕረግ ከመሾማቸው አስቀድሞ በተለያዩ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል። በኦሮሚያ የፀጥታ ዘርፍ ኀላፊ እንዲሁም የፌደራሉ ፖሊስ ምክትል ኮምሽነር ሆነው ሰርተዋል። በትግራዩ ጦርነት ሲጀመር የመከላከያ ሚንስትር የነበሩት ቀንዓ በመሀል በአብርሃ በላይ መተካታቸው ይታወሳል። የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚንስትር በነበሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተይዞ የነበረው የዋና አማካሪነት ቦታ እስካሁን አልተተካም። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) መካከል ኢትዮጵያ በጠየቀችው ብድር ዙሪያ አኹንም "ልዩነቶች" እንዳሉ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ አልቫሮ ፒሪስ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ድርድሮች እንደቀጠሉ መኾኑን የገለጡት ሃላፊው፣ ከድርድሮቹ አወንታዊ ውጤት እንጠብቃለን ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር በመደገፍ አስፈላጊነት ዙሪያ ባብዛኛው ስምምነት እንዳለ ሃላፊው መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል። ኢትዮጵያ ከድርጅቱ የጠየቀችው ብድር 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሲኾን፣ ከዓለም ባንክም ሌላ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ትጠብቃለች።

2፤ ኢዜማ፣ በዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ግፊት የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ታሳቢ ውሳኔን አምርሮ እንደሚቃወም ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኢዜማ፣ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ከሚያስገኘው ታሳቢ ጥቅም ይልቅ በዜጎች የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣ ይችላል በማለት አስጠንቅቋል። የብር የመግዛት አቅም ቢዳከም የአገሪቱን የጊዜያዊ የውጭ ምንዛሬ ችግር ሊያቃልልና ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችልበት እድል አለ ብሎ እንደማያምንም ኢዜማ ገልጧል። ፓርቲው፣ መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም ለማዳከም ከመወሰኑ ወይም ከመስማማቱ በፊት፣ በውሳኔው አንድምታ ላይ ሰከን ብሎ እንዲያስብም ጠይቋል። ኢዜማ፣ የኢኮኖሚ ችግሩ ዋና መፍትሄ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱ የገበያውን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ እንዲጨምር ማድረግ እንደኾነም ጠቅሷል። ኢዜማ ይህን አቋሙን የገለጠው፣ መንግሥት ከዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ዋሽንግተን ውስጥ እያደረገ ባለው የብድር ድርድር የብርን የመግዛት አቅም እንዲያዳክም ሊገደድ እንደሚችል እየተጠበቅ ባለበት ሰዓት ላይ ነው።

3፤ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት በትግራይ ኃይሎችና በአማራ ክልል ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ውጥረት ሳቢያ 29 ሺህ የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቆቦ እና ሰቆጣ ከተሞች መፈናቀላቸውን ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። ወደ ቆቦ 23 ሺህ እንዲኹም ወደ ሰቆጣ 5 ሺህ 980 ተፈናቃዮች እንደገቡ የገለጠው ቢሮው፣ የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብሏል። የተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብና ውሃ እጥረት አጣዳፊ ምላሽ እንደሚፈልግና እስካኹን ለተፈናቃዮች እርዳታ እያቀርቡ የሚገኙት የተቀባይ ማኅበረሰቦች መኾናቸውንም ቢሮው ጠቅሷል። የፌደራሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ዛሬ የችግሩን መጠን የሚገመግም ቡድን ልኳል ተብሏል። ቢሮው፣ የፌደራል ጸጥታ ኃይሎች በአላማጣ፣ ወልዲያና ቆቦ በመሠማራታቸው፣ የከተሞቹ ጸጥታ የተረጋጋ መኾኑንና አላማጣንና ቆቦን የሚያገናኘው መንገድም መከፈቱን ቢሮው ጠቅሷል።

4፤ "ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች" የተሰኘ የመብት ተሟጋች ድርጅት፣ በጦርነቱ ወቅት ከሥራቸው የተባረሩ 1 ሺህ 200 የትግራይ ክልል ፖሊሶች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የፌደራሉ የሕገ መንግሥት ትርጉም አጣሪ ካውንስል የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ላስገባው አቤቱታ እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ሪፖርተር ዘግቧል። ድርጅቱ አቤቱታውን ባለፈው ጥር ወር ለካውንስሉ ያስገባው፣ የቀድሞው የትግራይ ክልል መንግሥት በፌደራል መንግሥቱ ውሳኔ ከፈረሰ በኋላ በጦርነቱ ከሕወሃት ጎን አልቆማችኹም ብሎ ፖሊሶችን ከሥራ ማባረሩ የሕገመንግሥት ጥሰት ነው በማለት ነበር። ድርጅቱ በአቤቱታው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተባረሩትን አንጋፋ ፖሊሶች ያለ ምንም ጡረታ ማስቀረቱን በአቤቱታው ላይ ጠቅሷል። ካውንስሉ በበኩሉ፣ ተደራራቢ አቤቱታዎች እንዳሉበት ገልጦ፣ አቤቱታ አቅራቢው ድርጅት ውሳኔውን እንዲጠባበቅ ማሳሰቡን ዘገባው አመልክቷል። ድርጅቱ ግን፣ ጉዳዩ አንገብጋቢ የሕገመንግሥት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኾኑን ጠቅሶ፣ ካውንስሉ በቶሎ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ጠይቋል ተብሏል።

5፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ፣ ዛሬ ከፌደራል ግዛቶች መሪዎች ጋር በአወዛጋቢው የሕገመንግስት ማሻሻያ ዙሪያ ሊያደርጉት የነበረውን ውይይት ለሌላ ጊዜ አስተላልፈዋል። የፑንትላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ደኒ፣ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ በጠሩት ውይይት ላይ እንደማይገኙ ቀደም ብለው አስታውቀው ነበር። ፕሬዝዳንቱ ውይይቱን የጠሩት፣ አወዛጋቢውን የሕገመንግሥት ማሻሻያ ካጸደቁት በኋላ ነው። የሕገመንግስት ማሻሻያው፣ የአገሪቱን የመንግሥት አወቃቀር ከፓርላሜንታዊ ወደ ፕሬዝዳንታዊ አወቃቀር የሚቀይርና ጎሳን መሠረት ባደረገው የምርጫ ሥርዓት ምትክ ቀጥተኛ የምርጫ ሥርዓት እንዲኖር የሚደነግግ ነው። ፑንትላንድ ማሻሻያው አሳታፊ ውይይት ሳይደረግበት ጸድቋል በማለት፣ ከሳምንታት በፊት ከፌደራል መንግሥቱ መውጣቷ አይዘነጋም። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢዜማ፣ የመንግሥት አመራሮች፣ ካድሬዎችና የሜዲያ ተቀጣሪዎች "ሐሰተኛ መረጃ" እና "የጥላቻ ንግግር ሊባሉ የሚችሉ" ንግግሮችን በፌስቡክ ላይ በማሠራጨትና ስም በማጥፋት ዘመቻ ስለመጠመዳቸው ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ መረጋገጡ፣ "ፍጹም ተቀባይነት የሌለው" እና ሥልጣን ከያዘ መንግሥት የማይጠበቅ ድርጊት መኾኑን ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኢዜማ፣ ይህ "አምባገነናዊነት" እና ራስን "በአሸዋ መሠረት" ላይ የማቆም አካሄድ የዲሞክራሲ እንቅፋት በመኾኑ በጥብቅ አወግዘዋለሁ ብሏል። ፓርቲው፣ መንግሥት ከመሰል ድርጊቱ እንዲቆጠብና ለእስካኹኑ ድርጊቱ ሕዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቅ አሳስቧል። ፓርቲው፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን መንግሥትንና ፓርቲን በማይለዩ ሃላፊዎች በመያዛቸው ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣና ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን የመጀመሪያ የመረጃ ምንጭ አድርጎ እንዲቆጥር ተደርጓል ብሏል።

2፤ የቡድን-7 አገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች፣ በኢትዮጵያ የሰፈነው ውጥረትና ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር መግቢያ ስምምነት እንደሚያሳስባቸው ትናንት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። አገራቱ፣ ኢትዮጵያ እና ሱማሊያ "ኹሉንም የንግግር መስመሮች" ክፍት በማድረግ ውጥረቶችን እንዲያደርግቡ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የኢኮኖሚ ቀውስና የምግብ ዋስትና ማሽቆልቆል አሳሳቢ እንደኾኑም አገራቱ ገልጸዋል። የቡድኑ አባል አገራት፣ የመንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዘላቂ እንዲኾን፣ ሲቪሎችን ከጥቃት እንዲጠበቁ፣ ውጥረቶች በፖለቲካዊ ንግግር እንዲፈቱ፣ እርቅ፣ የሽግግር ፍትህና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥሪ አድርገዋል።

3፤ በተያያዘ ዜና የቡድን-7 አገራት፣ ሱማሊያና ኢትዮጵያ በባሕር በር መግቢያ ዙሪያ የገቡበትን ውጥረት ለመፍታት "ኹሉንም የንግግር መስመሮች ክፍት እንዲያደርጉ" ላቀረቡት ጥሪ፣ የሱማሊያ መንግሥት ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ ባወጣው መግለጫ አሉታዊ ምላሽ ሰጥቷል። የሶማሊያ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ከሰሜናዊቷ ግዛቴ ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችበትን የባሕር በር መግቢያ የመግባቢያ ስምምነት እስካልሰረዘችና የሱማሊያን አንድነት፣ ሉዓላዊነትና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርህ ሙሉ በሙሉ እስካላረጋገጠች ድረስ፣ ንግግር ማድረግ የሚሳካ ነገር አይደለም ብሏል።

4፤ የዓለም ጤና ድርጅት፣ አዲስ የኮሌራ በሽታ ክትባት ሥራ ላይ እንዲውል ማጽደቁን ትናንት ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። በአፍ በፈሳሽ መልክ የሚወሰደው ክትባት አኹን በጥቅም ላይ የሚገኘውን የኮሌራ ክትባት በማሻሻል የተመረተ እንደኾነ ድርጅቱ ገልጧል። አዲሱ ክትባት በዓለም ላይ በብዛትና በፍጥነት ለማምረት እንዲቻል ኾኖ የተዘጋጀ ነው ተብሏል። ኢትዮጵያ ባኹኑ ወቅት በኮሌራ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ ከተጠቁና ወረርሽኙ ረጅም ጊዜ ከቆየባቸው አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ናት።

5፤ የዓለም ጤና ድርጅት "ጆንሰን ኤንድ ጄንሰን" በተባለው የሕጻናት ሲረፕ መድኃኒት ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ ሊያወጣ እንደሚችል መናገሩን ሮይተርስ ዘግቧል። ድርጅቱ ይህን የገለጠው፣ ናይጀሪያ "ቤኒሊን" በተሰኘው የ"ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን" የሲረፕ ዓይነት ላይ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን አግኝቼበታለኹ በማለት ባለፈው ሳምንት ክትባቱን ማገዷን ተከትሎ ነው። መርዛማው ንጥረ ነገር፣ በጋምቢያ፣ ካሚሮን፣ ኢንዶኔዥያና ኡዝቤኪስታን ከዓመት በፊት ለ300 ሕጻናት ሞት ምክንያት እንደኾነ ዘገባው አስታውሷል። መርዛማ ንጥረ ነገር የተገኘበት ሲረፕ፣ "ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን" ኩባንያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያመረተው ነው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ዓርብ ሚያዝያ 11/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ መንግሥት፣ በጅምላና ችርቻሮ የወጪና ገቢ ንግድ የሚሠማሩ የውጭ ባለሃብቶችንና ኩባንያዎችን የሚከታተል ኮሚቴ ማቋቋሙን የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሃና አርአያሥላሴ ትናንት ይፋ አድርገዋል። ኮሚቴው፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር፣ ከገቢዎች ሚንስቴር እና ከብሄራዊ ባንክ የተውጣጡ አባላትን ያካተተ ነው። የኮሚቴው ሃላፊነት፣ ለወጪ ምርቶች ዝቅተኛውን ዋጋ መወሰን፣ በውጪ ገበያዎች ላይ ጥናት ማድረግና ፍትሃዊ ውድድርን ማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጧል። በተያያዘ፣ በወጪ ንግድ የተሠማሩ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች ለራሳቸው በሚይዙት የውጭ ምንዛሬ መጠን ላይ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚችል ኮሚሽነር ሃና መጠቆማቸውን ፎርቹን ዘግቧል።

2፤ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በትግራይ እና አማራ ክልሎች መካከል ሰሞኑን የተፈጠረው ውጥረት በአገራዊ ምክክሩ ሂደቱ እና በኮሚሽኑ እቅዶች ላይ ትልቅ እንቅፋት እንደሚፈጥር ስጋቱን ለሸገር ሬዲዮ ገልጧል። የኮሚሽኑ አንዱ ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ፣ ኹለቱ ክልሎች ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አድርገዋል። ኹለቱ ክልሎች ልዩነታቸውን ወደ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንዲያመጡትም ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ ጠይቀዋል። አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ወደ ትግራይ እና አማራ ክልሎች በመሄድ ያልጀመራቸውን ሥራዎች ለማከናወን አቅዶ እንደነበር የጠቀሱት ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ፣ ኹለቱ ክልሎች ወደ ግጭት የሚያመሩ ከኾነ ግን የኮሚሽኑ እቅዶች በከፍተኛ ደረጃ እንደሚስተጓጎሉ ተናግረዋል።

3፤ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ "የሚዲያ ሠራዊት" አባላት በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እና አሳሳች የፌስቡክ ዘመቻ ሲሳተፉ እንደቆዩ ቢቢሲ በምርመራ ማረጋገጡን ዘግቧል። ፓርቲው በተለይ በአዲስ አበባ ያደራጃቸው የሜዲያ አባላቱ፣ መንግሥትን በሚተቹና በሚቃወሙ ግለሰቦች ላይ ፌስቡክ ላይ ሐሰተኛ መረጃና ‘የጥላቻ ንግግር’ ሊባሉ የሚችሉ ጽሑፎችንና ምስሎችን እንደሚያሠራጩና የአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ አመራሮች ጭምር የመንግሥትን ገጽታ ለመገንባት ፌስቡክ ላይ በሚደረጉ አሳሳች ዘመቻዎች ላይ እንደሚሳተፉ ምርመራው ማረጋገጡን ዘገባው አመልክቷል። ሜታ ኩባንያ፣ በድርጊቱ የተሳተፉ ሐሰተኛ አካውንቶችን እና ገፆችን ቀደም ብሎ እንደደረሰባቸውና ርምጃ እንደወሰደባቸው መግለጡን ዘገባው ጠቅሷል። ገዥው ፓርቲ ግን፣ "የሜዲያ ሠራዊት" የተባለ አደረጃጀት እንደሌለው ገልጦ ድርጊቱ እንዳልተፈጸመ አስተባብሏል ተብሏል።

4፤ የገንዘብ ሚንሰትር አሕመድ ሺዴ የመሩት የመንግሥት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክና ከዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር መወያየቱን ሚንስቴሩ ዛሬ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። ውይይቱ የተደረገው ከአይ ኤም ኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክርስታሊና ጂኦርጄቫ እና ከዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንትና የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ ሃላፊ ቪክቶሪያ ክዋክዋ እንዲኹም ከሌሎቹ የኹለቱ ተቋማት ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር እንደኾነ ሚንስቴሩ ገልጧል። ውይይቱ፣ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ መንግሥት የተረጋጋ አገራዊ ጥቅል ኢኮኖሚ ለመገንባት እየወሰዳቸው ስላሉ ማሻሻያዎች፣ ስለ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ምርታማነትን ስለማሳደግ እና ስለ ግሉ ዘርፍ እንደሆነ ሚንስቴሩ ጠቅሷል። ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በጠየቀው የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ዙሪያ የተያዘው ወር ከመጠናቀቁ በፊት ዋሽንግተን ላይ ሌላ ዙር ድርድር እንደሚደረግ ቀደም ሲል መግለጡ አይዘነጋም።

5፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ መንግሥት ያቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ ባለፉት ቀናት ከሳዑዲ ዓረቢያ ባስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የነበሩ 4 ሺህ 200 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ወደ አገራቸው መመለሱን አስታውቋል። የሚንስቴሩ ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ብሄራዊ ኮሚቴው ፍልሰተኞቹን ያጓጓዘው በ12 የአውሮፕላን በረራዎች እንደኾነ ተናግረዋል። ብሄራዊ ኮሚቴው ከሳምንት በፊት በጀመረው መርሃ ግብር፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ወደ አገራቸው ለመመለስ ያቀደው 70 ሺህ ፍልሰተኞችን ነው። የሚንስቴሩ ቃል አቀባዩ፣ የኢትዮጵያና ሳውዲ ዓረቢያ የጋራ የሚንስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት በቀጣዩ ግንቦት ወር እንደሚካሄድም ተናግረዋል።

6፤ "ሴታዊነት- ለጾታ እከልነት" የተሰኘው ሲቪክ ማኅበር፣ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ከመተግበሩ በፊት በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ሊቆሙ፣ በግጭት ሳቢያ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንደገና ሊጀመሩና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሊመለሱ እንደሚገባ ለዋዜማ በላከው መግለጫ አሳስቧል። ማኅበሩ፣ በግጭቶች ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው አካላት በሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ትግበራ የሚኖራቸው ሚና ውስን እንዲሆን፣ ሲቪል ማኅበራትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዓለማቀፉ ኅብረተሰብ አካላት በፖሊሲው ትግበራ ሂደት "የክትትል" እና "ግምገማ" ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ትግበራ "ግልጽና ውስን የጊዜ ወሰን" እንዲኖረውም ጠይቋል። ማኅበሩ፣ በጾታዊ ጥቃቶች ዙሪያ ካቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች መካከል፣ የመንግሥት አካላት በግጭት ወቅት ለፈጸሟቸው ጾታዊና የወሲብ ጥቃቶች መንግሥት "እውቅና እንዲሰጥ" እና "ይቅርታ" እንዲጠይቅ የሚለው ይገኝበታል። 

7፤ አሜሪካ፣ ትናንት ከዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠለሉ 350 ስደተኞችን ወስዳለች። አሜሪካ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ከኢትዮጵያ ተቀብላ ለማስፈር ያቀደችው፣ ከ4 ሺህ 500 በላይ ስደተኞችን ነው። አይ ኦ ኤም፣ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ 5 ሺህ 304 ስደተኞችን በተለያዩ ሦስተኛ አገራት ማስፈሩን ገልጧል። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል፣ 1 ሺህ 194 የሚኾኑት ስደተኞች አሜሪካ ተቀብላ ያሠፈረቻቸው እንደኾኑ ድርጅቱ ባሠራጨው መረጃ አመልክቷል።

8፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ፍልስጤም የተመድ ሙሉ አባል እንድትሆን የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ ትናንት በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ ቢደግፍም፣ አሜሪካ ብቻ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብቷ የውሳኔ ሃሳቡን ውድቅ አድርገዋለች። የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረበችው አልጀሪያ ናት። አሜሪካ፣ ፍልስጤም የተመድ አባል በመኾኗ አስፈላጊነት ላይ ልዩነት እንደሌላት ገልጣ፣ ኾኖም አኹን ጊዜው አይደለም ብላለች። ከጸጥታው ምክር ቤት 15 አባላት መካከል 12ቱ የውሳኔ ሃሳቡን ሲደግፉት፣ ብሪታንያና ስዊዘርላንድ ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል። አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ባትጠቀም ኖሮ፣ ፍልስጤም በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ኹለት ሦስተኛ ድምጽ የድርጅቱ ሙሉ አባል ልትኾን ትችል ነበር። ከ193 የተመድ አባል አገራት፣ 139ኙ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና የሰጡ ናቸው። ፍልስጤም በጠቅላላ ጉባዔው ያላት መቀመጫ የታዛቢነት ነው። [ዋዜማ]
ከኤርትራ ጋር ያለንን ግንኙነት አሁን ባለበት ድንግርግር መንገድ መቀጠሉ ችግር አይደለም፣ ይልቁኑም በራሱ ጊዜ ወደ በጎ ሊቀየር የሚችልበት ዕድል ከፊታችን አለ ይላሉ የዋዜማ ከስምንተኛው ወለል እንግዳችን። ለቅምሻ ይህን ተመልከቱ፣
ለቸኮለ! ሐሙስ ሚያዝያ 10/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢዜማ፣ ፌደራል መንግሥቱ በፕሪቶሪያው ግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት የሕወሓት ታጣቂዎችን ባስቸኳይ ትጥቅ እንዲያስፈታ ጠይቋል። መንግሥት ሕወሃትን ትጥቅ ባለማስፈታቱ በሰዎችና ንብረት ላይ ለሚደርሰው ጉዳት “ሙሉ ኃላፊነቱን" እንደሚወስድ ፓርቲው አሳስቧል። ኢዜማ፣ የፓርቲነት ሕጋዊ እውቅና የሌለው ሕወሓት "የራሱን ታጣቂ ኃይል ያደራጀ ብቸኛ ስብስብ ኾኖ በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል” በማለት መንግሥትን ተችቷል። ፓርቲው፣ የፌደራል መንግሥቱ በጉዳዩ ላይ ያሳየውን ደካማ መረጃ አሰጣጥና ቸልተኝነት ተችቷል።

2፤ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ጄኔቫ ላይ ማክሰኞ'ለት በተካሄደው የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭት ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን ጨምሮ ኹሉንም የአገሪቱ ክፍሎች ረድኤት ድርጅቶች ያልተገደበና የማይቋረጥ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ለመፍቀድ መስማማቱን ገልጧል። መንግሥት የረድኤት ድርጅቶችን ሠራተኞች ደኅንነት ለማስጠበቅ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱት በፍቃደኝነትና ክብራቸውን በጠበቀ አኳኋን እንዲኾን፣ ለእርዳታ የሚውሉ መድሃኒቶችን ጨምሮ ከውጭ በሚገቡ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ላይ ቀረጦችን ለማንሳትና የረድኤት ሠራተኞችን የሺዛና የሥራ ፍቃድ አሰጣጥ ለማቀላጠፍ ቃል መግባቱም ተጠቅሷል። ማስተባበሪያ ቢሮው፣ መንግሥት በግጭት አፈታት፣ በአገራዊ ውይይትና በሽግግር ፍትህ ዙሪያ ከኹሉም አጋሮችና ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት ለመስራት መስማማቱንም አውስቷል። በዕለቱ ማሰባሰብ ከታሰበው 1 ቢሊዮን ዶላር የሰብዓዊ እርዳታ ገንዘብ ውስጥ ቃል የተገባው 630 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

3፤ በጃኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት፣ ማክሰኞ'ለት ለኢትዮጵያዊያን ተረጂዎች ገንዘብ ለማሰባሰብ ጄኔቫ ውስጥ በተካሄደው ዓለማቀፍ መርሃ ግብር ላይ የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞና ጩኸት ማሰማታቸውን አውግዟል። ፖሊስ ጩኸት ያሰሙትን ኢትዮጵያዊያን ይዞ ከአካባቢው እንዳራቃቸው ጽሕፈት ቤቱ ገልጧል። ጽሕፈት ቤቱ፣ ለድርቅ ተጎጂዎች ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ እርዳታ በሚያሰባስብበት መድረክ ላይ ጩኸት ማሰማት፣ የአገር ጠላትነት ፖለቲካ እንጂ የተቃውሞ ፖለቲካ አይደለም በማለት ተችቷል። የኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ ማኅበረሰብ፣ ባልተገባ ቦታ ጩኸት በማሰማት "አገር አዋራጅ" የኾነ ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ሊቃወማቸው እንደሚገባም ጽሕፈት ቤቱ አሳስቧል። ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤቱ፣ በአገር ክብር ላይ እጃቸውን የሚዘረጉ ግለሰቦችን በሕግ አግባባብ የምጠይቅበትን አሠራር እከተላለሁ በማለትም አስጠንቅቋል።

4፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅን ዛሬ ባደረገው ስብሰባ አጽድቋል። ምክር ቤቱ፣ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጁ የውጭ ኢንቨስትመንትን በቀላሉ ወደ አገሪቱ ለመሳብ፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና የአምራቹን ዘርፍ ይበልጥ ለማበረታታት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጧል። ረቂቅ አዋጁ፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን ለማቀላጠፍና አንዳንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ ዞን ለማሸጋገር ጭምር ያግዛል ተብሏል። አዋጁ፣ በተወሰኑ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባላቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ለመሰየምና ለማስተዳደር የሚያስችል ነው።

5፤ የሶማሊላንድ ራስ ገዝ የባሕር ጠረፍ ጠባቂ ፖሊስ 17 ኢትዮጵያዊያን ሕገወጥ ፍልሰተኞችን መያዙን የራስ ገዟ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኢትዮጵያዊያኑ ፍልሰተኞች የተያዙት፣ በሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በጀልባ ወደ የመን ሊሻገሩ ሲሉ እንደኾነ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ሰናግ በተባለው የግዛቲቷ አካባቢ በጠረፍ ጠባቂ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች መካከል፣ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል ተብሏል። ከሱማሊያ፣ ሶማሊላንድ ራስ ገዝና ጅቡቲ ወደ የመን በሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት የሚደረገው ፍልሰት፣ ለፍልሰተኞች ደኅንነት እጅግ አደገኛው እንደኾነ ዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በተደጋጋሚ ይገልጣል።

6፤ የኬንያ ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ፍራንሲስ ኦጎላ ዛሬ ኬንያ ውስጥ በደረሰ በሄሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን የአገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል። በወታደራዊ ሄሊኮፕተሯ ውስጥ ጀኔራል ኦጎላንና ሌሎች የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖችን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ተሳፍረው እንደነበር ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ጀኔራል ፍራንሲስ ኦጎላን የጦር ሠራዊቱ ዋና አዛዥ አድርገው የሾሟቸው ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ነበር።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ8022 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ9382 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ5744 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ9259 ሳንቲም ኾኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ4375 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ6463 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ሚያዝያ 10/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ በአዲስ አበባ ከተማ መሠረተ ልማትና የመሬት አጠቃቀም ዙሪያ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ትናንት መወያየታቸውን ገልጸዋል። ማሲንጋ፣ በአሜሪካ "ውስብስብና አንገብጋቢ" የፖለቲካ ጉዳዮች በኾኑት በከተማ እቅድና የከተማ መሠረተ ልማት ዙሪያ ገጥመዋት የነበሩትን ተግዳሮቶች ለአዳነች እንዳብራሩላቸው ጠቅሰዋል። በከተማ እቅድ ዙሪያ ከዜጎች ጋር ግልጽ ውይይት ማድረግን፣ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ እቅድ መንደፍንና በእቅድ አፈጻጸም ትዕግስት አስፈላጊ መኾኑን አሜሪካ ከልምዷ መማሯን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

2፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት፣ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ለመወያየት ጥያቄ አቅርቤያለሁ ማለቱን ዶይቸቨለ ዘግቧል። ምክር ቤቱ፣ ዐቢይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሶ፣ ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ጋር ጭምር እንዲወያዩ ጥያቄ እንዳቀረበ መግለጡን ዘገባው ጠቅሷል። ምክር ቤቱ ይህንኑ ጥያቄውን ከሦስት ሳምንት በፊት ለጠቅላይ ሚንስቴር ጽሕፈት ቤት ማስገባቱንና እስካኹን ምላሽ እየተጠባበቀ እንደኾነ ተናግሯል ተብሏል። ምክር ቤቱ ለውይይት ካነሳቸው አጀንዳዎች መካከል፣ የጋዜጠኞች እሥርና እንግልትና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የገጠሟቸው ችግሮች እንደሚገኙበት መጥቀሱንም ዜና ምንጩ አመልክቷል። ዐቢይ ላለፉት ስድስት ዓመታት ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ጋር ተወያይተው አያውቁም።

3፤ ፍትህ ሚንስቴር፣ የሚንስትሮች ምክር ቤት ትናንት በሙሉ ድምጽ ያጸደቀውን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዝርዝርና ወደፊት መከናወን ያለባቸውን ተግባራት በቀጣይ ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ይፋ አደርጋለኹ ብሏል። የሚንስትሮች ምክር ቤት በረቂቅ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ላይ ምን ዓይነት ማሻሻያዎችን እንዳደረገ ለጊዜው አልተገለጠም። ኾኖም የሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ከመጽደቁ በፊት፣ በርካታ አገር በቀል ሲቪል ማኅበራት ፖሊሲው የኤርትራ ወታደሮች በሰሜኑ ጦርነት የፈጸሟቸው ጥሰቶች "በልዩ ፍርድ ቤት" ይታዩ የሚለውን ጨምሮ መካተት አለባቸው ያሏቸውን በርካታ ምክረ ሃሳቦች ማቅረባቸው ይታወሳል።

4፤ አውሮፓ ኅብረት ለሱማሊያ ጸጥታ ማጠናከሪያ የ116 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማጽደቁን አስታውቋል። የኅብረቱ ምክር ቤት የፖለቲካና ጸጥታ ኮሚቴ ማክሰኞ'ለት ያጸደቀው የገንዘብ ድጋፍ፣ ለሱማሊያ ጦር ሠራዊትና ለአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ ወታደራዊ ክንፍ የተመደበ ነው። የገንዘብ ድጋፉ፣ የኅብረቱ የሰላም ሽግግር ተልዕኮ የጸጥታ ጥበቃውን ሃላፊነት በተያዘው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ለአገሪቱ ጦር ማስረከብ እንዲችል ያግዛል ተብሏል። ለአገሪቱ ጦር የተመደበው ከፊል ገንዘብ፣ ለቁሳቁሶች መግዣ የሚውል ሲኾን፣ ለኅብረቱ ተልዕኮ የተመደበው ገንዘብ ደሞ ለኅብረቱ ወታደሮች ደመወዝ ክፍያ ይውላል። [ዋዜማ]

View in Telegram

Telegram Channel