Ethiopia Insider Telegram Channel

Ethiopia Insider is a digital media that provides news, updates, analysis and features.

View in Telegram

Recent Posts

ምስላዊ መረጃ፦ ህገ ወጥ ድርጊት ፈጽመው በተገኙ “የነዳጅ ግብይት ተዋናዮች” ላይ የሚጣል የእስራት እና የገንዘብ ቅጣትን የያዘ የህግ ረቂቅ በትላንትናው ዕለት ለፓርላማ ቀርቧል። “የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ስርዓት ለመደንገግ” በተዘጋጀው በዚህ የአዋጅ ረቂቅ ላይ፤ ከ3 እስከ 7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶችን መወረስ ሊያስከትሉ የሚችሉ ህገ ወጥ ድርጊቶች ተዘርዝረዋል።

🛑 እስከ 7 ዓመት ጽኑ እስራት ከሚያስከትሉ ድርጊቶች መካከል አንዱ፤ የነዳጅ ውጤቶችን ሆን ብሎ ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብ” ነው።

🛑 ሌላው ከ3 እስከ 7 ዓመት ድረስ የሚያስቀጣ ወንጀል፤ “የነዳጅ ውጤቶችን ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ማጓጓዝ” ነው።

🛑 “የተረከባቸውን የነዳጅ ውጤቶች ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጪ ሲያጓጉዝ የተያዘ” እና “ከተፈቀደለት ማራገፊያ ውጪ ሲያራግፍ” የተገኘ ግለሰብም በተመሳሳይ ከ3 እስከ 7 ዓመት እስራት ይጠብቀዋል።

🛑 በእነዚህ ድርጊቶች የተሳተፈ ግለሰብ ሲያጓጉዛቸው የነበሩ የነዳጅ ውጤቶች እንደሚወረሱም የአዋጅ ረቂቁ ይደነግጋል።

🛑 “የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ያከማቸ፤ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው፣ ቦታ እና የግብይት ስርአት ውጪ ሲሸጥ የተገኘ ወይም በመመሪያ በተወሰነው መሠረት አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ” ግለሰብም፤ ከሚጣልበት ከ3 ዓመት የማይበልጥ ቀላል እስራት በተጨማሪ የተያዙበት የነዳጅ ውጤቶች ይወረሱበታል።

🛑 “አግባብ ካለው አካል በጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ፤ የነዳጅ ውጤቶችን የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ሲሸጥ የተገኘ” ሰውም እንዲሁ የተያዘበት የነዳጅ ውጤት ይወረስበታል። ይህን ድርጊት ፈጽሞ የተገኘ ሰው፤ ከ6 ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት ይጠብቀዋል።

@EthiopiaInsiderNews
የ2017 በጀት የውጭ ምንዛሬ ግብይት ላይ የሚደረግ ማሻሻያን ታሳቢ አድርጎ እንዳልተዘጋጀ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናገሩ

የ2017 በጀት ሲዘጋጅ ብር ከዶላር አኳያ ያለውን የምንዛሬ ተመን የሚያዳክም ውሳኔ ተግባራዊ ይደረጋል በሚል ታሳቢ እንዳልሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ። በኢ-መደበኛው እና በባንኮች በሚደረገው ይፋዊ ምንዛሬ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያጠብ እርምጃን አስመልክቶ “የቀረበ ነገር የለም” ያሉት አቶ አህመድ፤ የፌደራል መንግስት በጀት የተዘጋጀው “የነበረው አካሄድ እንደሚቀጥል ታሳቢ ተደርጎ” መሆኑን አስታውቀዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፤ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 4፤ 2016 በተካሄደው የተወካዮች መደበኛ ስብሰባ ላይ ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። አቶ አህመድ ዛሬ ፓርላማ የተገኙት፤ ለፌደራል መንግስት የተመደበውን የ2017 በጀት አስመልክቶ ዝርዝር መግለጫ ለማቅረብ ነበር።

ሚኒስትሩ 40 ደቂቃ ገደማ ከፈጀው የዛሬው የበጀት መግለጫ ንግግራቸው ግማሹን ያዋሉት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት አስመዝግቧል ያሉትን “ስኬቶች” እና ያጋጠሙትን “ተግዳሮቶች” ለማስረዳት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት 3 ዓመታት ሲተገብረው የቆየው የመጀመሪያው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራም በዚህኛው የሚኒስትሩ የንግግር ክፍል በስፋት ተዳስሷል።

ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፤ ይቀርፋቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ  ተግዳሮቶች መካከል አንዱ “የውጭ ምንዛሬ እጥረት” መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የፌደራል መንግስት “የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀምን ለማሻሻል አስፈላጊ የሆኑ የማሻሻያ እርምጃዎች” እንደሚወስድም ጠቁመዋል።

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/13292/
ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ከረጅም ጊዜ በኋላ፤
በፓርላማ ያነሱት ጥያቄ
የፌደራል መንግስት ከቀጣይ ዓመት በጀቱ ውስጥ 139.3 ቢሊዮን ብር ያህሉን ለዕዳ ክፍያ መደበ

የኢትዮጵያ መንግስት ለ2017 ባዘጋጀው ረቂቅ በጀት፤ 139.3 ቢሊዮን ብር ያህሉን ለዕዳ መክፈያ እንዲውል መደበ። ከዕዳ ክፍያ በመከተል ከፌዴራል የመደበኛ እና ካፒታል ወጪ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት መንገድ፣ ትምህርት፣ መከላከያ፣ ጤና እንዲሁም ፍትህ እና ደህንነት ዘርፎች ናቸው። 

🔴 ለፌደራል መንግስት ለቀጣዩ ዓመት የተመደበው በጀት አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ መሆኑን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይፋ የተደረገው ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ነበር። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት አርብ ግንቦት 30፤ 2016 ባደረገው መደበኛው ስብሰባው ለ2017 በጀት ዓመት 971.2 ቢሊዮን ብር በጀት ማጽደቁንም አስታውቋል።

🔴 የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በፓርላማ በመገኘት ማብራሪያ የሚያቀርቡበት ይህ የበጀት መጠን፤ ከዘንድሮው በጀት በ21.1 በመቶ ወይም 169.56 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ነው።

🔴 ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበሩት በጀቶች እንደተስተዋለው ሁሉ፤ ከፌዴራል የመደበኛ እና ካፒታል ወጪ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ በመጀመሪያው ረድፍ የተቀመጠው ለዕዳ ክፍያ የተመደበው የገንዘብ መጠን ነው።

🔴 በ2017 በጀት ለመደበኛ ወጪ ከተመደበው ገንዘብ ውስጥ 52 በመቶውን የያዘው ዕዳ ክፍያ ነው። ለዕዳ ክፍያ የተመደበው የገንዘብ መጠን፤ የፌደራል መንግስቱ ለዋና ዋና ወጪዎች ከያዘው 734.51 ቢሊዮን ብር ውስጥም 18.97 በመቶ ድርሻ አለው።

➡️ ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/13289/

@EthiopiaInsiderNews
የፌደራል መንግስት በቀጣዩ በጀት ዓመት ለክልሎች የሚያከፋፍለው ድጎማ ምን ያህል ነው?

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ2017 ካጸደቀው የፌደራል መንግስት በጀት ውስጥ፤ ለክልሎች እና ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ የተመደበው የገንዘብ መጠን 222.6 ቢሊዮን ብር መሆኑ ለፓርላማ በቀረበ ሰነድ ላይ ተመልክቷል። የገንዘብ ድጋፉ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ8.6 ቢሊዮን ብር አሊያም የአራት በመቶ ጭማሪ አለው።

➡️ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የቀጣዩ በጀት ዓመት የገንዘብ ድጎማ ዝርዝር ውስጥ ሁለት አዳዲስ ክልሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተካትተዋል።

➡️ በነሐሴ 2015 ዓ.ም. በህዝበ ውሳኔ የተመሰረቱት የደቡብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች፤ በድጎማ ክፍፍሉ ዝርዝር በሚያገኙት የገንዘብ መጠን አራተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 15.2 ቢሊዮን ብር፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ 12.8 ቢሊዮን ብር የድጎማ ገንዘብ ተመድቦላቸዋል።

➡️ የፌደራል መንግስት ለክልሎች ከሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ፤ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ከፍተኛውን መጠን የሚያገኘው የኦሮሚያ ክልል ነው። በ2017 በጀት ዓመት ለኦሮሚያ ክልል የሚሰጠው የገንዘብ ድጎማ 74.8 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ የገንዘብ መጠን ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር በሶስት ቢሊዮን ብር ገደማ ከፍ ያለ ነው።

➡️ በሁለተኛነት የሚከተለው የአማራ ክልል 47 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ከፌደራሉ መንግስት የሚያገኝ ሲሆን ይህም ከዘንድሮው በ1.8 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያሳየ ሆኗል።

🔵 ዝርዝሩን ለማንበብ👉https://ethiopiainsider.com/2024/13283/

@EthiopiaInsiderNews
ሰላማዊ ሰልፍ በማስተባበራቸው በአዋሽ አርባ ታስረው ከቆዩ እስረኞች የተወሰኑት ወደ አዲስ አበባ ተዘዋወሩ

ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ የነበረን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያስተባብሩ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል አራቱ፤ ለሁለት ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆዩበት ከአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ከትላንት በስቲያ አርብ አመሻሽ ወደ አዲስ አበባ መዘዋወራቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የነበሩት እና ላለፈው አንድ ሳምንት በአዲስ አበባ ፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ በትላንትናው ዕለት ከእስር ተለቅቀዋል። 

▶️ በአዲስ አበባ ከተማ ህዳር 30፤ 2016 ሊካሄድ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ “የእርስ በእርስ ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም ይስፈን” የሚል መሪ ቃል ነበረው።

▶️ ሰላማዊ ሰልፉ ካነገባቸው ሶስት ዓላማዎች መካከል፤ የመከላከያ ሰራዊት “የአገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ሚናው ውጪ” በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከሚሳተፍባቸው “ደም አፋሳሽ ተግባሮች” ተቆጥቦ፤ “ወደ ጦር ሰፈር እንዲመለስ” መጠየቅ የሚለው አንዱ ነበር። 

▶️ ከሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ቀርተው የነበሩ አራት እስረኞች፤ ከትላንት በስቲያ አርብ ግንቦት 30፤ 2016 አመሻሹን ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

▶️ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ቅጽር ግቢ ወደሚገኘው የእስረኞች መቆያ የተዘዋወሩት የሰልፉ አስተባባሪዎች፤ የኢህአፓ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ፣ ጠበቃ አበራ ንጉስ፣ ዮሴፍ ተሻገር እና እዮብ ገብረ ስላሴ መሆናቸውን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

🔴 ለዝርዝሩ 👉https://ethiopiainsider.com/2024/13273/

@EthiopiaInsiderNews
ሀገር በቀሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፤ በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመው “የዘፈቀደ እስር” አሳስቦኛል አለ

በጋዜጠኞች፣ በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እንዲሁም በፖለቲከኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው “የዘፈቀደ እስር” እንዳሳሰበው “ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ” የተሰኘው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ገለጸ። እርምጃው “በአሳሳቢ ሁኔታ እየጠበበ የመጣውን የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የማፈን አዝማሚያን የሚያመለክት ነው” ብሏል ድርጅቱ።

➡️ ድርጅቱ ይህን ያለው ዛሬ አርብ ግንቦት 30፤ 2016 ባወጣው መግለጫው፤ በኢትዮጵያ በርካቶች ስለሚጋፈጧቸው እውነታዎች የዘገቡ እና አመለካከታቸውን ያንጸባረቁ ግለሰቦች ታስረዋል ብሏል።

➡️ የግለሰቦቹ መታሰር፤ መሰረታዊ የሆኑትን የሰብዓዊ መብቶች “በግልጽ የሚጥስ” መሆኑን በመጥቀስ ድርጅቱ ተችቷል።

➡️ የኢትዮጵያ መንግስት “በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚፈጽማቸውን ጥሰቶች” እንዲያቆም እንዲሁም የዜጎችን የመናገርና ሀሳባቸውን በነጻነት የመግለፅ መብት እንዲያከብር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አሳስቧል።

➡️ ድርጅቱ “ሀሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ በማድረጋቸው ምክንያት ታስረዋል” ያላቸውን ሁሉንም ግለሰቦች፤ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርቧል።

🔴 ሙሊ ዘገባውን ለማንበብ👉https://ethiopiainsider.com/2024/13269/

@EthiopiaInsiderNews
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባካሄደው የመልካም አስተዳደር ምዘና፤ የማዕድን ሚኒስቴር “ዝቅተኛ አፈጻጸም” ማስመዝገቡ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ያለውን “መልካም አስተዳደር አፈጻጸም” በተመለከተ ላለፉት 10 ወራት ባደረገው ምዝና፤ የማዕድን ሚኒስቴር “ዝቅተኛ አፈጻጸም” ማስመዝገቡን አስታወቀ። የማዕድን ሚኒስቴር አፈጻጸሙ ዝቅ ያለው፤ የተቋቋመበት አዋጅ “የተሟላ ስልጣን እና ኃላፊነት ለሚኒስቴሩ የማይሰጥ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል። 

▶️ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፤ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት በአዋጅ የተሰጣቸንው ተግባራት “ጥራት፣ ቅልጥፍ እና ግልጽነት ባለው መንገድ” እየሰሩ መሆናቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ስልጣን አለው።

▶️ ተቋሙ የማዕድን ሚኒስቴርን ጨምሮ በ15 የፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ ከየካቲት 3፤ 2015 ጀምሮ ለ10 ወራት የቆየ “የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም” ምዝና ማከናወኑ ተገልጿል። 

▶️ ተቋሙ ምዝነናውን ለማከናወን የተጠቀማቸው፤ “ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ ፍትሃዊነት፣ ለህግ ተገዢነት እና ውጤታማነት” የሚሉትን የመልካም አስተዳደር መለኪያዎች ነው። 

▶️ በእነዚህ መለኪያዎች የተሻሻለ አፈጻጸም በማምጣት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ የያዙት የገንዘብ፣ የትምህርት እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ናቸው። የግብርና፣ የጤና እና የፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተከታዮቹን ደረጃዎች አግኝተዋል።

▶️ “መሻሻል የሚገባው” በሚለው ምድብ በብቸኝነት የተቀመጠው የማዕድን ሚኒስቴር ነው።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/13258/

@EthiopiaInsiderNews
በአማራ ክልል ለአስር ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መፍትሔ እንዳላመጣ ኦፌኮ እና እናት ፓርቲ አመራሮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ኢዜማ ግን አዋጁ በክልሉ “የተወሰኑ መረጋጋት እንዲኖር አድርጓል” ሲል አስታውቋል።

➡️ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ በአማራ ክልል ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የወሰነው ሐምሌ 28፤ 2015 ነበር።

➡️ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ባደረገው ስብሰባው አዋጁን ለ4 ወራት አራዝሞታል። 

➡️ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጨማሪ የ4 ወራት ቆይታ በዚህ ሳምንት ቢጠናቀቅም፤ አዋጁ መነሳቱን በተመለከተ በመንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ ማረጋገጫ የለም። ይሁንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “ማብቃቱን” አስታውቋል። 

➡️ የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “የአስቸኳይ አዋጁ ምን ዓይነት ችግር ለመፍታት እንደታወጀ አይገባኝም። አዋጁ በታወጀበትም ባልታወጀበትም ጦርነት ቀጥሏል” በማለት ለውጥ አለማምጣቱን ገልጸዋል። 

➡️ የእናት ፓርቲ የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ አባል እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳዊት ብርሃኑ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “መፍትሔ ሳይሆን ይዞ የመጣው፤ ይበልጥ ግጭት፣ ጦርነት እና ቁርሾ ከፍ እንዲል ነው ያደረገው’’ ብለዋል።

➡️ የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ በአማራ ክልል “በከተማዎች መሃል ይደረጉ የነበሩ የጥይት ድምጾችን [ያስቆመ]፣ ንጹሃን ዜጎች ላይ ይደርሱ የነበሩ መከራዎች በተወሰነ መልኩ መረጋጋት እንዲኖር ያደረገ ነው” ባይ ናቸው።

🔴 ለዝርዝሩ 👉https://ethiopiainsider.com/2024/13248/
ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ለአራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብቃቱን ተከትሎ፤ በእስር የቆዩ ሰዎች ሊለቀቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰቧል። ኮሚሽኑ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 28፤ 2016 ባወጣው አጭር መግለጫ፤ “በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ” እና “ሌሎች ማህበረሰባዊ አገልግሎቶች” ወደነበሩበት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

▶️ ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በዛሬው መግለጫው፤ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምን በተመለከተ “ክትትል እና ምርመራ” ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል።

▶️ ክትትል እና ምርመራዎቹን መሰረት በማድረግም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራ ወቅት የተስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ክፍተቶችን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ማድረጉን ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

▶️ ኢሰመኮ በእነዚህ ሪፖርቶች ሲያቀርባቸው ከቆያቸው ምክረ ሃሳቦች መካከል፤ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ ተይዘው “ተአማኒ ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች እንዲሁም በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ከእስር እንዲለቀቁ” የሚጠይቀው ይገኝበታል።

▶️ ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫውም፤ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበር አውድ ውስጥ” በእስር ላይ እንዲቆዩ የተደረጉ ሰዎች እንዲለቀቁ በተመሳሳይ መልኩ ጠይቋል።

▶️ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን “መሰረታዊ የሰብአዊ መብት መርህዎች ሊጣሱ አይገባም” የሚል አቋሙን በቀደሙ መግለጫዎቹ ሲያስተጋባ የቆየው ኢሰመኮ፤ ለአዋጁ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ በማብቃቱ “ወደ መደበኛው የህግ አተገባበር ሂደት መመለስ” እንደሚገባ በዛሬው መግለጫው አሳስቧል።

@EthiopiaInsiderNews
በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አዲስ አበባን የወከሉ የባለድርሻ አካላት ወኪሎች የምክክር አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ አስረከቡ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በመወከል በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሲሳተፉ የቆዩ ተወካዮች፤ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ “ሊመከርባቸው ይገባሉ” ብለው የለዩአቸውን ጉዳዮች ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት አስረከቡ። ተወካዮቹ ለምክክር ካስያዟቸው አጀንዳዎች ውስጥ “የአዲስ አበባ ባለቤትነት እና አወቃቀር፣ የቋንቋ፣ የሰንደቅ አላማ እና የህገ መንግስት” ጉዳዮችን የተመለከቱ ይገኙበታል ተብሏል።

➡️ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 27፣ 2016 በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደ የርክክብ ስነ ስርዓት፤ ተወካዮቹ አጀንዳዎቹን በስምንት ርዕሰ ጉዳዮች በመከፋፈል ለምክክር ኮሚሽኑ እንዳቀረቡ ተገልጿል።

➡️ ከርዕሰ ጉዳዮቹ መካከል፤ “ታሪክ እና ትርክትን”፣ “የሃገረ መንግስት ግንባታ እና የሃገር አንድነትን”፣ “የአንድነት እና ብዝሃነትን” የሚመለከቱ የአጀንዳ ሃሳቦችን የያዙ እንደሚገኙበት ተነግሯል። 

➡️ አሁን በስራ ላይ ካለው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ጋር የሚያያዙ፣ ተወካዮቹ የተመረጡበት የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይን በቀጥታ የሚመለከቱ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ባላት የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ የአጀንዳ ርዕሰ ጉዳዮችም ለምክክር ከተመረጡት ውስጥ እንደሚገኙበት በሂደቱ የተሳተፉ ተወካዮች አስረድተዋል።

➡️ የተቋማት ግንባታ፣ የምጣኔ ሀብት፤ ማህበራዊ እና ባህል ርዕሰ ጉዳዮችም እንዲሁ በአጀንዳነት መያዛቸውን ተወካዮቹ አብራርተዋል።  

🔵 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/13231/

@EthiopiaInsiderNews
በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው ከነበሩ እስረኞች መካከል አስራ ዘጠኙ መፈታታቸው ተነገረ

በአፋር ክልል በሚገኘው አዋሽ አርባ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ በእስር ላይ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ጋዜጠኞች መካከል አስራ ዘጠኙ “የተሃድሶ ስልጠና’’ ከወሰዱ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ መለቀቃቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በተመሳሳይ ቀን ሌሎች 20 እስረኞች ከአዋሽ አርባ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የእስረኞች ማቆያ እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን እና ነገ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።

▶️ እስረኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በዋነኛነት በአማራ ክልል እና እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት እንዲኖረው ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ነው።

▶️ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ባወጣው መግለጫ፤ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ወደሚገኝ “መደበኛ ያልሆነ ማቆያ ጣቢያ” የተወሰዱ እስረኞች ብዛት 53 መሆናቸውን አስታውቆ ነበር።

▶️ ኢሰመኮ፤ ከእስረኞቹ መካከል የኢዜማ የቀድሞ አባል የሆኑት መምህር ናትናኤል መኮንን እና ጋዜጠኛ አብነት ታምራት ከእስር መለቀቃቸውን ማረጋገጡን በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ስራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

▶️ በኢሰመኮ የነሐሴ ወር ሪፖርት ተጠቅሰው የነበሩት የቀድሞው የባልደራስ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ግንቦት 25 ከአዋሽ አርባ ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደተዘዋወሩ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

🔴 ለዝርዝሩ👉https://ethiopiainsider.com/2024/13219/

@EthiopiaInsiderNews
የተወካዮች ምክር ቤት ህወሓት ዳግም ህጋዊ እውቅና ሊያገኝ የሚችልበትን የአዋጅ ማሻሻያ አጸደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድጋሚ እንዲመዘገብ የሚፈቅድ አዋጅ አጸደቀ።

➡️ በ2011 ዓ.ም. የወጣውን “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅን” የሚያሻሽለው የህግ ረቂቅ የጸደቀው በሁለት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጸ ተዐቅቦ፣ በአብላጫ ድምጽ ነው።

➡️ “በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበሩ” የፖለቲካ ፓርቲዎችን “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገቡ የሚያስችለው የህግ ማሻሻያ፤ የፖለቲካ ቡድኖቹ ሊያሟሉ የሚገባቸው መስፈርቶችን እና የምርጫ ቦርድን ኃላፊነት የዘርዘረ ነው።

➡️ ይህ የአዋጅ ማሻሻያ፤ “ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል” በሚል “ህጋዊ ሰውነቱ እንዲሰረዝ” የተደረገው ህወሓት በድጋሚ እንዲመዘገብ የሚያስችሉ አንቀጾችን በውስጡ ይዟል።

➡️ “አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል ዛሬ የጸደቀው አዋጅ ደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews
“በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ” የፖለቲካ ፓርቲ፤ “በልዩ ሁኔታ” ለመመዝገብ ማመልከቻ ባቀረበ “በ15 የስራ ቀናት ውስጥ ምዝገባው እንዲፈጸም” የሚያደርግ አዋጅ ነገ በፓርላማ ሊጸድቅ ነው።

➡️ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩ ምዝገባ እና በዚህ ጉዳይ ላይ ምርጫ ቦርድ የሚኖረውን ስልጣን የሚወስኑ ድንጋጌዎች የተካተቱት፤ ይህንኑ በተመለከተ በ2011 ዓ.ም የጸደቀን አዋጅ ለማሻሻል በቀረበ የህግ ረቂቅ ላይ ነው።

➡️ የተወካዮች ምክር ቤት ነገ ማክሰኞ ግንቦት 26 በሚኖረው መደበኛ ስብሰባው ከሚመለከታቸው ጉዳዮች አንዱ ይኸው የአዋጅ ማሻሻያ እንደሆነ በስብሰባ አጀንዳ ማሳወቂያ መልዕክቱ ላይ አስፍሯል።

➡️ የተወካዮች ምክር ቤት አዋጁ ለውይይት እንዲቀርብ ቀጠሮ የያዘው፤ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራሩ ወጣ ባለ መልኩ የህግ ረቂቁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተመራለት በ3 ቀናት ጊዜ ውስጥ ነው።

➡️ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ የአዋጅ ረቂቅ፤ በነባሩ አዋጅ የተካተቱ 3 አንቀጾች ላይ ብቻ ማሻሻያ የሚያደርግ ነው።

ከማሻሻያዎቹ መካከል፦

⭕️ “አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” የሚለው ይገኝበታል።

⭕️ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ መልኩ የቀረበለትን ማመልከቻ ውድቅ የማድረግ አማራጭ በአዋጁ ባይሰጠውም፤ በፓርቲው ላይ ለሁለት ዓመታት “ክትትል እና ቁጥጥር” የማድረግ ስልጣንን ግን ያገኛል።

🔴ዝርዝሩ 👉https://ethiopiainsider.com/2024/13159/

@EthiopiaInsiderNews
የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ፤ ስለ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ኃላፊነት ምን ይላል?

በ1995 ዓ.ም. የወጣውን የኢሚግሬሽን አዋጅ የሚያሻሽል የህግ ረቂቅ በትላንትናው ዕለት ለፓርላማ ቀርቧል። አዋጁን ለማሻሻል ካስፈለገባቸው ምክንያቶች “አንዱ የተቀናጀ ድንበር ቁጥጥር አስተዳደርን” አስመልክቶ ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ተግባራዊ ካደረገው መመሪያ ጋር የኢትዮጵያን ስርዓት ማጣጣም በማስፈለጉ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

የዓለም አቀፉ ድርጅቱ ተግባራዊ ያደረገው መመሪያ፤ ሀገራት የመንገደኛ ቅደመ ጉዞ መረጃ እና ምዝገባ ስርዓትን እንዲዘረጉ የሚያስገድድ ነው። ኢትዮጵያ የዚህ መመሪያ ፈራሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ በመሆኗ፤ ይህንኑ ስርዓት በኢሚግሬሽን ማሻሻያ አዋጅ ላይ እንዲካተት መደረጉ በአዋጅ ማብራሪያው ላይ ተመልክቷል።

በዚህ መሰረት፦

▶️ ማንኛውም አጓጓዥ መንገደኛን ወደ ሀገር ለማስገባት ወይም ከሀገር ለማስወጣት ከማጓጓዙ ከ3 ሰዓት በፊት፤ የመንገደኛውን ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ስም ዝርዝር ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት የማሳወቅ ወይም የመላክ ግዴታ እንዲኖረው ተደርጓል።

▶️ ይህ መሆኑ “መረጃውን በመለዋወጥ የሚፈለጉ አደገኛ ወንጀለኞች በተለይም ሽብርተኞችን ጉዳት ሳያደርሱ በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ተብሏል።

▶️ “ማንኛውም ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ውጭ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ አጓጓዥ፤ በሀገራት መካከል በሚኖር በእንካ ለእንካ መርህ ወይም በሚደረግ ስምምነት መሰረት፤ የመንገደኞችን ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ስም ዝርዝር ወደሚሄድበት አገር ከመውሰዱ በፊት እንዲያሳውቅ ግዴታ ተጥሎበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews
ባለፉት 9 ወራት ለዓለም ገበያ የቀረበው የማዕድን መጠን ምን ያህል ነው?

ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለዓለም ገበያ ካቀረበቻቸው ማዕድናት ከ13.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷን የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ሀብታሙ ተገኝ ትላንት አስታውቀዋል። ይህ የገንዘብ መጠን ከወርቅ ማዕድን የተገኘውን ገቢ አይጨምርም። ሀገሪቱ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያቀረበቻቸው ማዕድናት ዝርዝር የሚከተለው ነው፦

⭕️ ጌጣ ጌጥ - 79.55 ቶን

⭕️ ታንታለም ኦር - 69.8 ቶን

⭕️ የኢንዱስትሪ ማዕድናት - 32,141 ቶን

⭕️ ጥሬ እና እሴት የተጨመረበት ኦፓል - 19.9 ቶን

⭕️ ሊቲየም - 11, 176.4 ቶን

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/13147/

@EthiopiaInsiderNews
ባለፉት 9 ወራት ከማዕድናት ሽያጭ ማሳካት የተቻለው ገቢ፤ ለበጀቱ ዓመቱ ከታቀደው 56 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ማዕድናት 514 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ብታቅድም፤ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሶስት ገደማ ወራት ብቻ በቀሩት በዚህ ጊዜ ማሳካት የቻለችው 56 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ። ሀገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወርቅ ያገኘችው የውጭ ምንዛሬ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ83 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተነግሯል።

የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ሀብታሙ ተገኝ የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 22፤ 2016 ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ከተናገሩት:-

➡️ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቀረበ የወርቅ ምርት 274 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።

➡️ በእነዚህ ወራት ለብሔራዊ ባንክ ከገባው 3.023 ቶን የወርቅ ምርት ውስጥ አብዛኛውን ያቀረቡት በወርቅ ማውጣት የተሰማሩ ኩባንያዎች ናቸው።

➡️ ባለፉት 9 ወራት የተመረተው የወርቅ መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር “የ12.6 በመቶ ብልጫ ያሳየ ነው”

➡️ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ወርቅን ጨምሮ ከማዕድናት የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 289 ሚሊዮን ዶላር መሆኑንም ተናግረዋል።

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/13147/

@EthiopiaInsiderNews
ዜጎች ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ስልጣንን ለኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ኃላፊ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀረበ

ማንኛውንም ሰው ከሀገር ውስጥ እንዳይወጣ የማገድ ስልጣንን፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመራ ኃላፊ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀረበ። የአዋጅ ማሻሻያው፤ በህገ ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጪ ሀገር ዜጎች “በጥቁር መዝገብ እንዲመዘግቡ እና ከሀገር እንዲወጡ” የሚያስችል “አስተዳደራዊ ቅጣት” የመጣል ስልጣንን ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ይሰጣል።

➡️ እነዚህን አዲስ ድንጋጌዎች ያካተተው የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ የተላለፈው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ነው።

➡️ ሀገራት “ሉዓላዊ ስልጣንን” ተግባራዊ ከሚያደርጉባቸው ህጎች “በዋነኛነት” የሚጠቀስ ነው የሚባልለት የኢሚግሬሽን ህግ፤ “በህግ የተከለከሉ ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዳይወጡ እና ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ቁጥጥር የሚደረግበትን አግባብ” የሚደነግግ ነው።

➡️ በስራ ላይ ከዋለ 21 ዓመት የሞላው ነባሩ ህግ፤ “ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በህግ መሰረት በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ብቻ ነው” ይላል።

➡️ ዛሬ ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ በነባሩ ህግ የተቀመጠውን የፍርድ ቤት “ብቸኛ ስልጣን” የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመራ ኃላፊ በተጨማሪነት ያጋራ ሆኗል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/13135/

@EthiopiaInsiderNews
ቪዲዮ፦ የሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ ገና ላልተወሰነለት ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ “ቁልፍ ሚና ይኖረዋል” የተባለለት የምክክር ምዕራፍ፤ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 21፤ 2016 በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በይፋ ተጀምሯል። በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በተካሄደው በዛሬው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ 119 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ቁጥራቸው ከሁለት ሺህ በላይ የሚልቀው እነዚህ ተወካዮች፤ ለሀገር አቀፍ ጉባኤ የሚሆኑ የአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ምክክር ያደርጋሉ። በዚህ ምክክር የሚለዩ አጀንዳዎችን፤ በቀጣይ በሚከናወነው የሀገር አቀፍ ጉባኤ “አጀንዳ ቀረጻ” ወቅት እንዲካተቱ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህንኑ ኃላፊነቱን “በአግባቡ የሚወጣ መሆኑን” የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን በዛሬ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር “አዲስ ውጤት ለማግኘት፣ በአዲስ መንገድ መሄድ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ህዝቡ በተወካዮቹ አማካኝነት ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ፤ ስር የሰደዱ ችግሮችን ምንጭ ከመለየት ጀምሮ በምክክር ሂደቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እኩል የምተሳተፉበት እና አሻራችሁን የምታሳርፉበት ታሪካዊ መድረክ እነሆ ተፈጥሯል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ያደረጉትን ሙሉ ንግግር ለመመልከት ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://youtu.be/Gij2BZV3xgM

🔴 ዘገባውን በጽሁፍ ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/13131/

@EthiopiaInisderNews
በኢትዮጵያ በጎርፍ ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት ምን ያህል ነው?

በኢትዮጵያ ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከ590 ሺህ በላይ ሰዎች መጠቃታቸው እና 95 ሺህ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት ባለፉት ቀናት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በጎርፍ የተጠቁት አካባቢዎች የሚገኙት በዘጠኝ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሆናቸውንም የተቋማቱ ሪፖርት አመልክቷል።

ከክልሎች መካከል በጎርፍ ብርቱ ጉዳት ያስተናገደው የሶማሌ ክልል መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) አስታውቋል። በክልሉ በአፍዴር፣ ሊበን እና ሸበሌ ዞኖች የሚገኙ አካባቢዎች በጎርፍ በመጥለቅለቃቸው ከ247 ሺህ ሰዎች በላይ መጠቃታቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። በእነዚህ ዞኖች ቢያንስ 51 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንም ጽህፈት ቤቱ ይፋ አድርጓል።

በሶማሌ ክልል የሚገኙት የሸበሌ፣ ገናሌ እና ዌብ ወንዞች ከግንቦት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ መቀነስ ቢያሳዩም፤ በአካባቢው ሊጥል በሚችለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ወንዞቹ ሊሞሉ ስለሚችሉ አሁንም ክትትል እንደሚያስፈልግ የመንግስታቱ ድርጅት ጽህፈት ቤት በሪፖርቱ አሳስቧል። በሶማሌ ክልል ባለፈው ጥቅምት እና ህዳር ወር በነበረው የዝናብ ወቅት፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጎርፍ ተጠቅተው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ የነበረው ጎርፍ በመሰረተ ልማቶች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በርካታ ከብቶችንም ለሞት ዳርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews
See more posts

View in Telegram

Telegram Channel
TeleSearch Telegram Search